በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት መታሰቢያ ነገ በሐረሪ ክልል ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት መታሰቢያ ነገ በሐረሪ ክልል እንደሚካሄድ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሄኖክ ሙሉነህ እንደገለፁት÷ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያ “መቼም አንረሳውም” በሚል መሪ ቃል በክልሉ ደረጃ ታስቦ ይውላል፡፡
መታሰቢያው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ጀግንነትና መስዋዕትነት ምልክት አድርጎ ለመወሰድ ያለመ ነው ማለታቸውን የጽሕፈት ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
መታሰቢያው በተለይም በትምህርት ቤቶች፣ በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚካሄድ ሲሆን÷ ዕለቱም ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ በማድረግ እና ደም በመለገስ ይታሰባል፡፡
ነገ ከቀኑ አራት ሰዓት በሚካሄደው መታሰቢያ የክልሉ ሕዝብ ቀኝ እጁን በደረቱ ላይ በማድረግ እና አሽከርካሪዎች ደግሞ ለአንድ ደቂቃ ክላክስ በማሰማት ለመከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ድጋፍ እዲገልጹ ጥሪ ቀርቧል፡፡