Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የተደረሰው የሠላም ስምምነት ተፈጻሚ ሆኖ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስት እና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሠላም ስምምነት ተፈጻሚ ሆኖ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ፡፡

በመንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የሠላም ስምምነት አስመልክቶ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት መግለጫ ሰጥቷል፡፡

መግለጫው በመንግስትና በህወሓት መካከል ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተደረሰው የሠላም ስምምነት በሀገራችን ውስጥ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ሚናው እጅግ የጎላ ነው ብሏል።

ጦርነት ጎጂና የማያስፈልግ መሆኑን፣ በተለይም በወንድማማች ሕዝቦች መካከል የሚደረግ ጦርነት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ቀውስ ከማስከተሉም በላይ በህዝቦች መካከል መቃቃርን የሚፈጥርና መልሶ ለመጠገን ጊዜ የሚወስድ መሆኑን በመረዳት ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሠላም መስፈን በዓለም አቀፍ መድረኮች በተከታታይ ድምጿን ስታሰማ ቆይታለች ነው ያለው።

በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነትም ጦርነቱ ቆሞ ዘላቂ ሠላም እንዲወርድ የተደረሠው ስምምነት ከምንጊዜውም በላይ በችግር ውስጥ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን የሠላምና ተስፋ እንዲፈነጥቅ የሚያደርግ ነው፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ÷ የተፈጠረው የሠላም ስምምነት ተፈፃሚ እንዲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጠይቋል።

ለተደረሠው የሠላም ስምምነት መርሆ ሁሉም ተገዢ በመሆን ለጋራ ሀገር በጋራ አንድ ሆኖ መጓዝ እንደሚገባም አስገንዝቧል።

በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖች ተገቢውን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ከማድረግ ጀምሮ የህዝብ ለህዝብ ግንኙቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አበክረን እንሰራለን ሲልም ክልሉ ያለውን ዝግጁነት በመግለጫው አረጋግጧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.