አርቲስት አሊ ቢራ የትውልዶች ሁሉ ማስተማሪያ ነው -የሙዚቃ ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የክብር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ የትውልዶች ሁሉ ማስተማሪያና በጥበብ ስራዎቹ ራሱን አስከብሮ የኖረ ነው ሲሉ የሙዚቃ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ የሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት ይፍሩ፣ የሙዚቃ ባለሙያው ሰርጸፍሬ ስብሀትና ሌሎች የሙዚቃ ባለሙያዎች በክብር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ የአስከሬን ሽኝት መርሐ ግብር ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዶክተር ዳዊት ይፍሩ በመልዕክታቸው÷ አርቲስት አሊ ቢራ ጥበብ እንዴት እንደሚሰራ፣እንዴት እንደሚጻፍና እንደሚቀርብ አሳይቶናል፣ ትልቅ ትምህርትም ሰጥቶናል ነው ያሉት።
አሊ ቢራ ንፉግ አደለም ያሉት ዶክተር ዳዊት÷ ስለዚህ የአሊ ቢራን ፈለግ መቀበል ያለበት ትውልድ አለን፣ ይህ ትውልድ ጥበብን አውጥቶ ለኢትዮጵያ ህዝብ በነጻ ትርጉም ያለው ስራ መስጠት አለበት ብለዋል፡፡
የሙዚቃ ባለሙያው ሰርጸፍሬ ስብሀት በበኩላቸው÷ አርቲስት አሊ ቢራ የትውልዶች ሁሉ ማስተማሪያ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
አርቲስት አሊ ቢራ የራሱን ሙዚቃዎች ራሱ ሲጽፍና ሲያቀናብር እንደነበር ጠቅሰው÷ በዚህ ልክ የተሰፉ የሀገራችን ድምጻውያን በቁጥር ጥቂት መሆናቸውን አንስተዋል።
ቀልድ የሚያውቅ ታላቁንም ታናሹንም የሚያከብር ልዩ የጥበብ ሰው ነበር ያለው ደግሞ÷ድምጻዊ መሐሙድ አህመድ ነው፡፡
አርቲስት አሊ ቢራ ለህዝብ በርካታ የጥበብ ስራዎችን በነጻ ያበረከተ ነው ያሉት ሌሎች የሙዚቃ ባለሙያዎች ÷ጥበብ ብዙ ጊዜ ገንዘብ ታፈራለች ይባላል፣ የዚህን ትሩፋት ግን አሊ ቢራ ያገኘ አይመስለንም ብለዋል፡፡
በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ያለን ሰዎች በሙሉ ያለንን በነጻ ለህዝብ ካበረከትን ከኢትዮጵያ ህዝብ የምናገኘው መልስና ክብር እንደዚህ መሆን አለበት ሲሉም ነው የገለጹት።
አሊ ቢራ በጥበብ ራሱን አስከብሮ የኖረ ነው ያሉት የሙዚቃ ባለሙያዎቹ÷ አሁንም አስከሬኑ ወደ መቃብር በክብር ይሸኛል፣ ስራዎቹም በክብር ለረጅም ጊዜ ይኖራሉ ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡
አንጋፋ አርቲስቶች ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያበረክቷቸውን የጥበብ ስራዎች መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው÷ አርቲስቶችን ሲሞቱ ብቻ ሳይሆን ሲታመሙም መንከባከብ ማሳካም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
የሙዚቃ ባለሙያዎች ለአርቲስት አሊ ቢራ ቤተሰቦች፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ለሙያ አጋሮቹ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
በየሻምበል ምህረት