በ1 ቢሊየን ብር ወጪ የሚከናወነው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የማጠናቀቂያ ስራ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) መመዘኛዎችን መሰረት በማድረግ በአንድ ቢሊየን ብር ወጪ የሚከናወነው ቀሪ የማጠናቀቂያ ስራ ተጀምሯል፡፡
የስታዲየሙ ሁለተኛ ዙር ሥራዎች የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተገለጸው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት 700 ሚሊየን ብር ለስታዲየሙ ማጠናቀቂያ የመደበ ሲሆን÷ ቀሪው 300 ሚሊየን ብር ደግሞ በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ድጋፍ የሚሸፈን ይሆናል፡፡
በሁለተኛው ዙር ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል÷ የሜዳ ጥራት ማሻሻያ፣ የእንግዳ መቀበያ ክፍል፣ መቀመጫ ወንበር መግጠም እና መሰብሰቢያ አዳራሽ እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡
የማጠናቀቂያ ሥራው የፊፋ መመዘኛ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ የሚሠራ ሲሆን÷ ይህም ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ወደ ማስተናጋድ እንዲመለስ ያሥችለዋ ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሁለተኛው ዙር ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም መመዘኛ መስፈርቶችን ባለሟሟላቱ ምክንያት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ ማገዱ ይታወሳል።
ይህም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ማስተናገድ የሚያስችል የተሟላ ስታዲየም እንዳይኖራት በማድረጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላለፈው አንድ ዓመት ጨዋታውን ከሀገር ውጪ እንዲያደርግ ተገዷል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!