ተጨማሪ 9 ሀገራት ዓለም አቀፉን ድንበር ተሻጋሪ የንፋስ ኃይል ጥምረት ተቀላቀሉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብፅ ሻርም ኤል ሸክ እየተካሄደ በሚገኘው 27ኛው የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ተጨማሪ 9 ሀገራት የዓለም አቀፉን ድንበር ተሻጋሪ የንፋስ ኃይል ጥምረት መቀላቀላቸው ተሰምቷል፡፡
ጥምረቱን የተቀላቀሉት ዘጠኝ ሀገራትም ÷ ቤልጂየም ፣ ኮሎምቢያ ፣ ጀርመን ፣ አየርላንድ ፣ ጃፓን ፣ ኔዘርላንድስ ፣ ኖርዌይ ፣ ብሪታኒያ እና አሜሪካ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ሀገራቱ በአማራጭ የንፋስ ኃይል አቅርቦት ላይ በመሥራት የዓየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ያግዛሉ መባሉን የዓለም አቀፉን የታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ መረጃ ዋቢ አድርጎ የዘገበው አናዱሉ ነው፡፡
በዓለም አቀፉ የታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ፣ በዴንማርክ እና በዓለም አቀፉ የንፋስ ኃይል ምክር ቤት ሐሳብ አመንጪነት ዕውን የሆነው የንፋስ ኃይል ጥምረት ÷ መንግስታትን ፣ የግሉን ዘርፍ ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በማሰባሰብ የንፋስ ኃይል አማራጭን ይበልጥ ለማስፋት እንደሚያስችል ታምኖበታል።
አሁን ላይ ከንፋስ የሚገኘውን 60 ጊጋ ዋት ኃይል እስከ ፈረንጆቹ 2050 ድረስ ከ2 ሺህ ጊጋ ዋት በላይ ለማድረስ ታስቧል፡፡