ኮሚቴው በዓየር የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ የሚያስችለውን የሙከራ በረራ ዛሬ ወደ ሽረ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከሁለት ዓመት በኋላ የመጀመሪያ የሆነውን የአውሮፕላን የሙከራ በረራ ዛሬ ወደ ሽረ አውሮፕላን ማረፊያ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ኮሚቴው በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ ÷ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ከሁለት ዓመት በኋላ የመጀመሪያው የሆነው የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አውሮፕላን የሙከራ በረራ ዛሬ ወደ ሽረ ማድረጉን ገልጿል።
ወደ ትግራይ የሚደረጉ የአየር በረራዎች እንደገና መጀመራቸውም አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታን በፍጥነት ወደ ክልሉ ለማድረስ ያግዛል ነው ያለው፡፡
ይህም አፋጣኝ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን በርካታ ሰዎች ስቃይ ለመቅረፍ እንደሚረዳ አንስቷል፡፡
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር የአስቸኳይ ጊዜ እና የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ለመስጠት የሚያስችሉ የህክምና ቁሳቁስ የያዙ ሁለት ተሽከርካሪዎች ትናንት መቐለ መድረሳቸውን የሚታወስ ነው፡፡
መቐለ የደረሱት መድሃኒቶች አስቸኳይ የህክምና ድጋፍ ለሚሹ ሰዎች እንደሚውሉም ነው ማህበሩ የገለጸው።