ከ513 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከሕዳር 2 እስከ 8 ቀን 2015ዓ.ም ባደረገው ክትትል ከ513 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን አስታወቀ፡፡
በዚህም 483 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት ገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን እና ከ30 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ወጭ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በድምሩ 531 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ናቸው በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽኅፈት ቤቶች የተያዙት፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን ሲያዘዋዉሩ የተገኙ 21 ግለሰቦች እና 17 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው የጉሙሩክ ኮሚሽን ያስታወቀው፡፡
ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሐኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ ዕቃዎች ፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ ዕፆች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
ገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት አዲስ አበባ ኤርፖርት ፣ ድሬዳዋ እና ቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽኅፈት ቤቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡