አቶ ደመቀ መኮንን መንግስት የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገለፁ
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 14 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከናይጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄፍሬ ኤንያማ ጋር ኒያሚ ውስጥ በሁለትዮሽና አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በኒያሚ በተጀመረው የአፍሪካ ህብረት 17ኛ ልዩ ስብሰባ እየተሳተፉ ያሉት አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እና በፕሪቶሪያ ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ለሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚ እንዲሆን ፅኑ ፍላጎት እንዳለው እና መንግስት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች ብለዋል።
የሰብአዊ ድጋፍና ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የጠቀሱት አቶ ደመቀ፥ የዳግም ግንባታና የመልሶ መቋቋም ተግባር ሌላው ትኩረት መሆኑንም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ፈተና በገጠማት ወቅት ናይጄሪያ በመርህ ላይ የተመሰረተ የማይዋዥቅ አቋም በማራመዷ አቶ ደመቀ ምስጋና ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦሌሴጉን ኦባሳንጆ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር እንዴት ራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ማሳየታቸውን በማንሳትም፥ እንደ አንጋፋ መሪም ከሌሎች ጋር በመሆን ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውንም ነው የተናገሩት።
የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ በመፈረሙ መደሰታቸውን ጠቅሰው፥ ውጤቱ አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ የመፍታት ብቃት እንዳላት የሚያሳይ መሆኑን አንስተዋል።
የናይጄሪያ መንግስት ለስምምነቱ ስኬታማ አፈፃፀም የሚቻለውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው 28 በመቶ የሚሆነውን የአፍሪካ የህዝብ ቁጥር በያዙት ኢትዮጵያና ናይጄሪያ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ወዳጅነትና ስትራቴጂካዊ የባለብዙ ወገን ትብብር እንዲጠናከር በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡