21 የዳያስፖራ አደረጃጀት ጥምረት አባላት የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ እየተከናወኑ ላሉ ጉዳዮች ድጋፋቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመላው ዓለም የሚገኙ 21 የዳያስፖራ አደረጃጀት ጥምረት አባላት ለሰላም ስምምነቱና ስምምነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ መንግሥት እየተከናወኑ ላሉ ጉዳዮች ድጋፋቸውን ገለጹ፡፡
የጥምረቱ አባላት ይህን የገለጹት ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የሀገራትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ሚዲያዎች በላኩት የአቋም መግለጫ ደብዳቤ ነው።
በአሜሪካ፣ አውሮፓና ካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አደረጃጀቶችን በመወከል መግለጫውን ያወጡት የጥምረቱ አባላት፥ በደቡብ አፍሪካና በኬንያ በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መካከል ለተደረሰው የሰላም ስምምነት እና አተገባበር ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ ዕውን እንዲሆን የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት ይቻላል የሚለውን መርህ በማራመድ የአፍሪካ ሕብረት ላበረከተው አስተዋጽዖና ለስምምነቱ ተግባራዊነት ለሚያሳየው ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ሆኖም በውጭ ያሉ አንዳንድ አካላት፣ የአንዳንድ ሀገራት ፓርላማ አባላት እንዲሁም ሚዲያ እና ተቋማት የሰላም ስምምነቱን መንፈስ የሚያውክና ገንቢ ያልሆነ አስተያየት በመስጠት በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ ሕዝቦች በግጭት አዙሪት ውስጥ እንዲቆዩ የሚያደርጉት አፍራሽ እንቅስቃሴ እንዳሳዘናቸውም ነው የገለጹት፡፡
በአንጻሩ የተገኘውን የሰላም ዕድል በመጠቀም የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍና መሰረታዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት ለማቅረብ እያከናወናቸው ስላሉ ተግባራት አድናቆታቸውን ገልጸው÷ ህወሓትም ትጥቅ የመፍታት ቁርጠኝነቱን እንዲያሳይ ጠይቀዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም የአሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት የሰላም ሂደቱን በመደገፍ ከኢትዮጵያ ጋር ላላቸው ዘላቂ ግንኙነትና የጋራ ተጠቃሚነት ትኩረት እንዲሰጡ፣ የሰላም ሂደቱን ለማጨናገፍ እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም ነው የጠየቁት።
የህወሓት አመራሮችም የሰላም ስምምነቱን ለማስፈጸም ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ጥምረቱ ጠይቋል፡፡
በመላው ዓለም የሚገኙ የዳያስፖራ አባላትም የሰላም ሂደቱን ለመደገፍ የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው በመቀጠል በግጭት ምክንያት የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለማሰባሰብ እንዲሠሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!