ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና የፌደራል የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በጋራ ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 16 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና የፌደራል የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሙስናን ለመከላከል በጋራ መስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የፌደራል የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (እና የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ናቸው።
ተቋማቱ የተፈራረሙት ስምምነት በሀገሪቱ ሙስናን ለመከላከል የሚደረገውን ንቅናቄ በሚዲያ ዘርፍ ለማገዝ ያስችላል ተብሏል።
የፌደራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ መንግስት በአሁኑ ሰዓት ሙስና የሀገር ብሄራዊ ስጋት መሆኑን ገምግሞ ለመቀነስ ትልቅ ስራ እየሰራ በሚገኝበት ሰዓት ስምምነቱ መፈረሙ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
የተጀመረውን የፀረ ሙስና ትግል በማጠናከር ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የምርመራ ጋዜጠኝነት ስራዎችን እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር መፈራረሙ ህዝቡ የተለያዩ ብልሹ አሰራሮችን እንዲጠቁም ያስችለዋልም ነው ያሉት።
ሙስናን መታገል የሚቻለው የዜጎችን አመለካከት በመቀየር ሲሆን ትውልድን ለመገንባትም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተሻሉ ስራዎችን እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ በበኩላቸው ኮሚሽኑ በትክክለኛው ሰዓት ትክክለኛ ሚዲያ እንደመረጠ ተናግረዋል።
በቅርቡ የምርመራ እና የዘጋቢ (ዶክመንተሪ) ጋዜጠኝነት ዳይሬክቶሬት በመክፈት የተለያዩ የምርመራ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል ።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ብልሹ አሰራሮች የሚጋለጡበት በእውነት እና በእውቀት የሚሰራ የሚዲያ ተቋም መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በሃይለማሪያም እና መሳፍንት እያዩ