ኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ግንባታ ተሞክሮዋን አካፈለች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ “በአፍሪካ ኅብረት የመሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮግራም ሥር የምስራቅ አፍሪካ ክልላዊ ፕሮጀክቶች እና ቻይና በሚል በተዘጋጀ የውይይት መርሐ ግብር የኢትዮጵያን ተሞክሮ አካፍለዋል።
በመርሐ ግብሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በኢትዮጵያ ያሉትን የመሰረተ ልማት አቅሞች እንዲሁም ለሀገራዊና ክልላዊ ኢኮኖሚ ልማት ያላቸውን ጠቀሜታ አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የግሉን ዘርፍ የኢንዱስትሪ ልማት ሞተር አድርጎ በመውሰድ፣ የግብርና መር ኢንዱስትሪያላይዜሽንን በመከተል፣ ኤክስፖርት ተኮር አውቶሜሽን ላይ በማተኮር እንዲሁም ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ነድፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂው በመንገድ፣ በባቡር፣ በአየር፣ በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በኤሌክትሪክ ሃይል እና በውሃ አቅርቦት እንዲሁም ለባለሃብት በሚሰጥ መሬት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የ10 አመት እቅድ ለሚቀጥሉት አስርት አመታት የኢነርጂ ሴክተሩን በማሳለጥ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት እና ለቀጣናዊ ውህደት በተለይም ለምስራቅ አፍሪካ እድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ጠቁመው ጂቡቲን፣ ሱዳንንና ኬንያን ተጠቃሚ በማድረግ ጥርጊያው የተጀመረ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በመጨረሻም መንግስት የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ለውጭ ባለሃብቶች ምቹ ለማድረግ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማዘጋጀት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሰ መሆኑንም አምባሳደር ተሾመ መናገራቸውን ከቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡