Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል የሀገር አቋራጭ እና የከተማ ውስጥ የህዝብ ትራንስፖርት ታገደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችሉ የተለያዩ ውሳኔዎች ማሳለፉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ወደ ጋምቤላ ከተማ የሚገቡም ሆነ የሚወጡ ከፍተኛና መለስተኛ ሀገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ ለ14 ቀናት እንዲቆም ተወስኗል ብለዋል፡፡

ከክልሉ ርዕሰ ከተማ ወደ ሁሉም የክልሉ ዞንና ወረዳዎች የሚደረጉ የህዝብ ማመላለሻ ከመጫን አቅማቸው 50 በመቶ ቀንሰው ህዝብ እንዲያመላልሱም ውሳኔ ተላልፏል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የከተማ የህዝብ ማጓጓዣ ባጃጅ፣ ሚኒባስና ሌሎች የህዝብ ማጓጓዣዎች ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 14 ቀናት የታገደ ሲሆን የመንግስትም ይሁን የግል ሞተር ሳይክሎች ከአሽከርካሪው በስተቀር ሰው መጫን ተከልክሏል ነው የተባለው፡፡

እንዲሁም ጭፈራ ቤቶች፣ ጫት ቤቶችና ሺሻ ቤቶች የቫይረሱን ተጋላጭነት ስለሚጨምሩ ሙሉ በሙሉ እንዲዘጉ የተወሰነ ሲሆን ወደ ክልሉ ምንም ዓይነት ጫት እንዳይገባ ተወስኗል፡፡

በርካታ የመንግስት ሰራተኞች ያሉባቸው መስሪያ ቤቶች ሰራተኛን በመቀነስ እንዲሁም በእድሜ የገፉ፣ ህፃናት የሚያጠቡና ነፍሰ ጡር እናቶች ቤታቸው ሆነው ስራ እንዲሰሩም ነው ውሳኔ የተላለፈው፡፡

በክልሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ የሚገኝ ሲሆን ከበሽታው የመተላለፍ ባህሪና በክልሉ ያሉት ስደተኞች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ በመሆናቸው ይህንን ሥጋት መፍትሔ ለመስጠት የፌደራል መንግሥት ከስደተኞች አስተዳደር ህግ አንፃር ለሥጋቱ መፍትሄ የሚሆን ውሳኔ እንዲሰጥ ተገቢውን መረጃ ለመለዋወጥ ውሳኔ ወስኗል፡፡

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.