ከአውቶቡስ ተራ – መሳለሚያ- 18 ቁጥር ማዞሪያ የመንገድ ግንባታ በጊዜው እንዳይጠናቀቅ የወሰን ማስከበር ሥራ እንቅፋት ሆኗል – መንገዶች ባለስልጣን
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአውቶቡስ ተራ – መሳለሚያ- 18 ቁጥር ማዞሪያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ የወሰን ማስከበር ሥራ እንቅፋት እንደሆነበት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ገለጸ፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢያሱ ሰሎሞን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ያለው መንገዱ 3 ነጥብ 35 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 40 ሜትር የጎን ስፋት አለው።
ከዚህ ፕሮጀክት ጋር የተጀመሩ ሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ አምስት ወራት እንደሆናቸው አስታውሰው፥ የዚህ መንገድ ግንባታ ግን በተያዘለት ጊዜ እየተከናወነ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመንገድ ግንባታ አፈጻጸሙ አሁን ላይ 16 በመቶ መሆኑን ጠቁመው፥ ለፕሮጀክቱ መጓተትም በዋናነት የወሰን ማስከበር ሥራዎች ሙሉ በሙሉ አለመጠናቀቃቸውን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
740 ሜትር ያህሉ የመንገዱ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት ንጣፍ ተደርጎለት በከፊል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን እና 52 ሜትር ርዝመት ያለው ከመሳለሚያ ወደታች በሚገኘው ወንዝ ላይ ያለው የድልድይ ግንባታም አብዛኞቹ የስትራክቸር ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ከ140 በላይ ቤቶች፣ 113 የኤሌክትሪክ እና 34 የቴሌኮሙኒኬሽን ምሰሶዎች አለመነሳታቸው የፕሮጀክቱን ግንባታ እንዳይሳለጥ አድርገውታል ነው ያሉት፡፡
ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ያለው ሥራ ለፕሮጀክቱ ፈተና መሆኑን ጠቁመው፥ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ፕሮጀክቱ የሚገኝባቸው ክፍለ ከተሞች እና መሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን በፍጥነት ከሠሩ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ግንባታውን በፍጥነት ለማከናወን ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አንዱዓለም ይጥና ታደሰ በበኩላቸው፥ ከአውቶቡስ ተራ 18 ማዞሪያ ድረስ ያለው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በተጀመረበት ሰሞን መነሳት ያለባቸው ቤቶች ብዛት 612 እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
እስካሁን 545 ቤቶች መነሳታቸውን እና 67 ቤቶች መቅረታቸውን ጠቅሰው በዚሁ ወቅት አፈጻጸሙ 95 በመቶ እንደነበር አመላክተዋል።
ይሁን እንጅ በቅርቡ በመንገዶች ባለስልጣን በኩል በተደረገው ተጨማሪ ማሻሻያ ደግሞ 20 የቀበሌ ቤቶች እንዲነሱ እና 10 ማስተካከያ (ከፈረሰ በኋላ ከ10 እስከ 30 ሴንቲ ሜትር ማስተካከያ የሚደረግላቸው) እንዲሁም 6 ሠነድ አልባ ቤቶች እንዲፈርሱ መጨመራቸውንም ነው ያነሱት።
በመሆኑም ያልተነሱ እና መጠነኛ ማስተካከያ የሚደረግላቸው ቤቶች ብዛት 100 መድረሱን፤ ከካሣ ክፍያ ጋር በተያያዘ እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች ቢሆንም በየጊዜው የሚደረጉ ተጨማሪ ማሻሻያዎች የሚነሱ ቤቶችን ቁጥር ከፍ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡
እንደዚህም ሆኖ ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ያለው አፈጻጸም 83 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱን ጠቅሰዋል።
የካሳ ክፍያው ከተፋጠነ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ኮርፖሬሽንም የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚኒየም) የመረጡ ተነሽዎችን በአስቸኳይ ካስተናገደ ክፍለ ከተማው እስከ አንድ ወር ባለው ጊዜ ሙሉ በሙሉ ለማንሣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የመንገዶች ባለስልጣንም መሠረተ ልማት እና ቤቶች እስከተነሱበት ድረስ ባለው ቦታ ላይ ግንባታውን ማስቀጠል እንደሚችልም ጠቅሰዋል።
18 ማዞሪያ አካባቢ ያሉ ሰባት የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን ጨምሮ የውኃና ፍሳሽ መሠረተ ልማቶች በአጭር ጊዜ እንዲነሱ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁም ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በጉዳዩ ላይ እያከናወነ ያለውንና የደረሰበትን ሁኔታ እንዲያሳውቀን በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!