የአየር ንብረት ለወጥ መከላከል ስራዎችን ከሌሎች ሀገራዊ የልማት እቅዶች ጋር አስተሳስሮ የመተግበር ስራ እየተከናወነ ነው – ዶ/ር ፍጹም አሰፋ
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአየር ንብረት ለወጥን የመከላከልና ተጽዕኖን የማላመድ ስራዎችን ከሌሎች ሀገራዊ የልማት እቅዶች ጋር አስተሳስሮ የመተግበር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ በወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩትን ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አኒ ዳንጎታ የተመራ የልኡካን ቡድንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሚኒስትሯ ÷የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረሰ መሆኑን እና መንግስት ለመከላከል ስራው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በአስር ዓመቱ የመንግስት የልማት እቅድ ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራ አንድ የእቅዱ ስትራቴጅክ ምሰሶ ሆኖ መካተቱን አንስተዋል፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጅን በመንደፍ ተግባራዊ መድረጉንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በአየር ብክለት ላይ ያላት ድርሻ እጅግ አናሳ ቢሆንም ባደጉት ሀገራት ከፍተኛ ብክለት እደረሰባት ያለው ጉዳት ግን ሀገሪቱን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር ፍጹም ከዚህ ቀደም በየአስር ዓመቱ ሚከሰተው ድርቅ አሁን ላይ በየሶስት ዓመቱ መከሰት መጀመሩንና ጎርፍና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን ተከትለው በሚመጡ ችግሮች ኢትዮጵያ እተፈተነች መሆኑን አንስተዋል።
በቅርቡ የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ የበካይ ጋዝ ልቀት ልማት ስትራቴጂን ይፋ ያደረገቺው ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ቁርጠኛ አቋም ከማረጋገጥ በላይ ተጨባጪ ለውጦችን አምጥታለችም ብለዋል።
የወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አኒ ዳንጎታ በበኩላቸው÷ 25 ቢሊየን ችግኞችን በአራት ዓመታት መትከል መቻል ለዓለም ሀገራት ምርጥ ተሞክሮ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡
ለዚህ ተገባር የወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት እውቅና የሚሰጠው መሆኑን ጠቁመው÷ የአየር ንብረት ተፅዕኖንና የተሰሩ የመከላከል ስራዎች የሚያመጡትን ለውጥም በተመለከተ ሳይንሳዊ መረጃ በማጠናቀር ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አቡዳቢ በሚደረገው ሃያ ስምንተኛው የአየር ንብረት ጉባኤ ተሳትፎ እንዲሁም በሌሎች ትብብር መስኮች ላይ ሰፊ ምክክር መደረጉም ተጠቁሟል፡፡
የተጀመሩ የመረጃ ማጠናቀር ድጋፎች በሰው ሃይል አቅም ግንባታ እና መሰል ትብብር መስኮች ላይ የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር ከስምምነት መደረሱንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡