በጅማ፣ ሀሮማያና ነቀምቴ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ማዕከላት በሚቀጥለው ሳምንት ስራ ይጀምራሉ
አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 1፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል ጅማ ፣ሀሮማያና ነቀምቴ ከተሞች የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ማዕከላት በሚቀጥለው ሳምንት ምርመራ ይጀምራሉ።
በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽንን ለመከላከል ክልሎች የኮረና ቫይረስ መመርመሪያ ላቦራቶሪዎችን እና ቫይረሱ የተገኘባቸዉን መንከባከብ የሚያስችሉ የተለያዩ ማእከላት በተለያዩ ከተሞች በመቋቋም ላይ ይገኛሉ።
በቅርቡም የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እነዚህን ማእከላት በክልሉ ላይ ለማስፋት መንግስት ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎ የአዳማዉ መመርመሪያ ማእከል ባለፈዉ ማክሰኞ ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል።
በጅማ ፣ ሀሮማያ እና ነቀምቴ ከተሞች በግንባታ ላይ ያሉት ማእከላት በሚቀጥለዉ ሳምንት ወደ ስራ እንደሚገቡ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የስራ ሀላፊዎቹ ገልጸዋል።
በነዚህ ከተሞች በአሁኑ ጊዜ ግንባታቸዉ እየተጠናቀቀና ባለሞያዎችም ስልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙም ነው የተጠቆመው፡፡
ከዚያም ባለፈ ከተለያዩ አካላት ለምርመራው የሚረዱ ቁሳቁሶችም እጃቸዉ የማስገባት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ለጣቢያችን ተናግረዋል።
የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ጤና እና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ዳይሬክተሩ ዶ/ር ያደታ ደሴ ÷በሀሮማያ ለምርመራው የሚረዱ ሁለት ማሽኖች ተከላ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የመመርመር እና የህክምና አገልግሎቱን ለህዝቡ ከገለጽን በኋላ በሚቀጥለዉ ሳምንት እናስጀምራለን ነው ያሉት።
አያይዘውም ማዕከሉ ወደ ስራ ሲገባም በቀን እስከ 700 ሰው መመርመር ይችላል ብለዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሃመድ አባመጫም በበኩላቸዉ የተከላ ሂደቱ የተጠናቀቀው ሁለት ማሽን ለአገልግሎት ተዘጋጅተዋል።
በቫይረሱ ለተገኘባቸው የሚያገለግሉ 200 አልጋዎች እና ለተጠረጠሩት የሚያገለግልም 3 ሺህ አልጋዎች ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል ። የሰዉ ሀይልም ቢሆን በዚህ ሳምንት ስልጠናቸዉን አጠናቀዉ ወደ ስራ ይገባሉ።
የወለጋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ሀሰን የሱፍ በነቀምቴም ለምርመራዉ የሚያገለግሉ 6 ማሽኖች ተከላ መጠናቀቁን ጠቁመው÷ ከዚህ ቀደም የነበሩትን ማሽኖች የማሰናዳት ስራ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ማዕከሉ የባለሞያና የቁሳቁስ ዝግጅት በዚህ ሳምንት አጠናቆ በሚቀጥለዉ ሳምንት መጀመሪያ ወደ ስራ እንደሚገባ ዶክተር ሀሰን ገልጸዋል፡፡
በአፈወርቅ አለሙ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision