የህዳሴ ግድብ ባለብዙ ቀጠናዊ ጥቅሞች ተምሳሌታዊ ፕሮጀክት ነው- ሱዳናዊ ተንታኝ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፋሰሱን ብሎም የቀጠናውን ሃገራት ጥቅሞች የሚያስጠብቅ ምሳሌ የሚሆን አፍሪካዊ የልማት ፕሮጀክት ነው ሲሉ ሱዳናዊው የቀድሞ ዲፕሎማት ጋዜጠኛ እና ተንታኝ መኪ አልሞግራቢ ገለጹ።
መኪ አልሞግራቢ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአካባቢ ጥበቃ መርሆዎች ጋር የተስማማ እና በሃይል ልማት መስክ የአህጉሪቱን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚያፋጥን አይነተኛ መሳሪያ ነው ብለዋል።
ግድቡ የሃይል እጥረትን ለማቃለል፣ ቀጠናዊ ምጣኔ ኃብታዊ ትስስርን ለማጠናከር እና ቁልፍ ኃይል ተጠቃሚ የልማት እንቅስቃሴዎችን ለማፋጠን እንደሚያግዝም ገልፀዋል።
በተጨማሪም ለሃገራቸው ሱዳን ጎርፍ የሚያስከትለውን አደጋ እና ስጋት በመቀነስ እንዲሁም ደለልን አስቀርቶ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል የተጣራ እና የተመጠነ ውሃን ተደራሽ በማድረግ አይነተኛ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥም አመላክተዋል።
የግድቡን ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ይዘትና ቅርፅ ለመስጠት የሚደረጉ ሙከራዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ጠቅሰው ብቸኛው የልዩነት መፍቻ መንገድ በኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል የሚደረገው ውይይት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካን እውነቶች ለቀሪው ዓለም ለማስረዳትም ሆነ እንደ ህዳሴው ግድብ የመሳሰሉ ትላልቅ ቀጠናዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ከውጫዊ ጫናዎች ለመከላከልም አህጉራዊ ሚዲያ እጅግ አስፈላጊ ነው። ስለሆነም ለተፈፃሚነቱ ሁሉም አፍሪካዊ የበኩሉን ሊወጣ ይገባልም ነው ያሉት።
የግድቡን የግንባታ ሂደት ለሶስት ጊዜ መጎብኘታቸውን በማንሳትም መቼም ቢሆን በፕሮጀክቱ ዙሪያ ያላቸው ቀና አመለካከት እንደማይቀየርም አስረድተዋል።
ግድቡ ለመላው አፍሪካውያን ኩራት የሆነ ሃብት መሆኑን በመጥቀስም ሱዳናውያንም ሆኑ ሌሎች አፍሪካውያን ከእርሳቸው ጋር የተቀራረበ ሃሳብ እንዲኖራቸው ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ነው የሚገልጹት።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት ጋር በተያያዘ ባነሱት ሃሳብም በቅርቡ ኢትዮጵያ እንደነበሩ በመጥቀስ፥ ጦርነቱ ካቆመ እና የሰላም ስምምነቱ ከተደረሰ ወዲህ የመጡትን ለውጦች መታዘብ መቻላቸውን አመላክተዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች እየተነቃቁ እንደሆነ መታዘባቸውን በማንሳት ነገሮች ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት ሆኔታ እየተመለሱ እንደሆነ ማስተዋላቸውን ይጠቅሳሉ።
ከኢትዮጵያ እና ከሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በሰነዘሩት ሃሳብ የሃገራቱ መሪዎች ችግሮችን በንግግር ለመፍታት እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን በማጠናከር እና በሁለቱ ሃገራት የንግድ ማህበረሰብ አባላት ምጣኔ ኃብታዊ ትስስሮችን በማጎልበት የጋራ ተጠቃሚነትን ማስፈን እንደሚቻልም ገልፀዋል።
በወንደሰን አረጋኸኝ