ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት እና ፈረንሳይ ጋር የ32 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ተፈራረመች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት እና ፈረንሳይ ጋር የ32 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ተፈራርማለች፡፡
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ፣ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ቫለሪ ቴሂዮ እና የአውሮፓ ህብረት ትብብር የኢትዮጵያ ኃላፊ ስቴፋን ሎክ ተፈራርመውታል፡፡
ድጋፉ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ለግብርና ማገገሚያ የሚውል መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።
ፕሮጄክቱ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አማካኝነት የሚተገበር ሲሆን፥ ገበሬዎች የግብርና ስራቸውን ዳግም እንዲጀምሩና የመሰረተ ልማት አገልግሎቶችን ዳግም ስራ ለማስጀመር ይውላል ነው የተባለው።
በድጋፉ የሚተገበረው ፕሮጄክት በእነዚህ አካባቢዎች የግብርና ምርታማነትን ዳግም በማነቃቃት አስቸኳይ ድጋፍ ለሚሹት ጉዳዮች ምላሽ የመስጠት እና በኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የማጠናከር ዓላማን ያነገበ መሆኑ በዚህ ወቅት ተገልጿል።
በሁለት ዙር ለሚተገበረው ፕሮጄክት ማስፈጸሚያም የፈረንሳይ የልማት ኤጄንሲ 18 ሚሊየን ዩሮ እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት 14 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አድርገዋል።
በመጀመሪያው ዙር 533 ሺህ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተሻሻለ የምርጥ ዘር፣ የዶሮ ዝርያዎች፣ የተመረጡ የወተት ላሞችና የርቢ በግና ፍየሎች፣ የአትክልትና አበባ ምርጥ ዘር አቅርቦት እና ለመስኖ ልማት የሚውሉ ውሃ መሳቢያ ፓምፖች ድጋፍ ይደረጋል ተብሏል።