የግብጽ መንግስት የአባይ ወንዝ ላይ የያዘውን አሉታዊ አቋም ቀይሮ ወደ ሥምምነት እንዲመጣ በዓለምአቀፍ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብጽ መንግስት የአባይ ወንዝ ላይ የያዘውን አሉታዊ አቋም ቀይሮ ወደ ሥምምነት እንዲመጣ በመላው ዓለም በሚገኙ ከ30 በላይ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ተጠየቀ፡፡
የዳያስፖራ አደረጃጀቶቹ የአባይ ወንዝ ፍትሃዊ አጠቃቀምን የሚደግፍና የግብጽ መንግስት ከዚህ አንጻር የያዘውን አሉታዊ አቋም በመቀየር ወደ ስምምነት እንዲመጣ የሚጠይቅ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
አደረጃጀቶቹ ለግብጽ ህዝብና መንግስት በላኩት መግለጫ ÷ በታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው ድርድር በትብብር መንፈስ የሚመራ፣ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚነት የሚያደርግ ሆኖ በፍትሀዊነትና እኩልነት የሚቋጭ እንዲሆን የግብጽ ህዝብና መንግስት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲወጡ ጥያቄ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያውያን ለመልማት ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ከራሳቸው ባሰባሰቡት ሐብት ከፍተኛ የውሃ ድርሻ በሚያበረክቱበት ወንዝ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያን ኅዳሴ ግድብ ላለፉት 12 ዓመታት ሲገነቡ መቆየታቸውንም መግለጫው አስታውሷል፡፡
የግድቡ መገንባት በሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት መካከል የሚኖር ትብብርንና ትስስርን የሚያሳድግ እንዲሁም የውሀ አስተዳደር ውጤታማነትን የሚጨምር ዕድል ይፈጥራልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ግድቡን አካባቢያዊና ቴክኒካዊ መመዘኛዎችን ባሟላ ሁኔታ በመገንባት ላይ መሆኗን የአቋም መግለጫው አንስቷል፡፡
መግለጫው ኢትዮጵያ በታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልኅ ጉዳት እንደማያደርስም በተደጋጋሚ ማረጋገጫዎችን ስትሰጥ መቆየቷንም አውስቷል፡፡
ግድቡ የሚገነባበበት ዋነኛ ዓላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማሳደግና ለአካባቢያዊ የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኃይል ስትራቴጂን ለማረጋገጥ ነው ብለዋል።
አደረጃጀቶቹ በደብዳቤያቸው ከግድቡ ጋር በተያያዘ ሲቀርቡ በነበሩ የተሳሳቱ መረጃዎች ምክንያት ግብጻውያን ስጋት ሊያድርባቸው እንደሚችል እንደሚረዱ ገልጸው ÷ እውነታው ሲታይ ግን ግድቡ ለግብጽም ሆነ ለሱዳን በበጋ ወቅት የውሀ ፍሰትን በመጨመርና በክረምት ጎርፍን በመቀነስ በርካታ ጠቀሜታዎችን የሚያስገኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አክለውም የአባይ ወንዝ የተፋፈሱ ሀገራት የሚጋሩት ሐብት መሆኑን እንደሚረዱ በመጥቀስ፥ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መፍትሄን እንደሚደግፉ አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም ግብጻውያን በግድቡ ላይ የሚቀርቡ የተሳሳቱ መረጃዎችን እንዲሞግቱ ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ማንም ላይ ጉልኅ ጉዳት ሳያደርሱ የተፈጥሮ ሐብታቸውን ተጠቅመው ለመልማት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የግብጽ መንግስት ደግሞ ከዛቻና ማስፈራሪያ ወጥቶ በግድቡ ላይ የሚደረገው ድርድር ፍሬያማ ውጤት እንዲያስገኝ በጎ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአረብ ሊግና አባል ሀገራቱ በማይመለከታቸው አፍሪካዊ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባታቸውን እንዲያቆሙም አሳስበዋል።
አደረጃጀቶቹ ደብዳቤያቸውን በየሚኖሩባቸው ሀገራት ለሚገኙ የግብፅ ኤምባሲዎች፣ የተለያዩ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ተቋማት በአካልና በኢሜል የሚያስገቡ ሲሆን፥ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የጀመሩትን የዲጂታል ዘመቻም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።