ከሳዑዲ ዓረቢያ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የመመለሱ ሒደት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሳዑዲ ዓረቢያ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የመመለሱ ሒደት መጠናቀቁን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ከመጋቢት 2014 በተጀመረው ዜጎችን የመመለስ ሒደት 131 ሺህ 642 ዜጎችን ወደ ሀገር መመለስ መቻሉን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ተልዕኮም በመንግስት 493 ሚሊየን ብር እና 50 ሚሊየን ብር ደግሞ በአጋር አካላት በድምሩ 543 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
ለተመለሾቹ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ የማድረግ ስራ መሰራቱንም አቶ ደበበ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲቀላቀሉም የመጡበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት አስፈላጊው የስነ ልቦና ምክር የተሰጣቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የስራ ፈጠራ እና የተለያዩ የክህልት ማጎልበቻ ስልጠናዎች የተሰጧቸው መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በመላኩ ገድፍ