Fana: At a Speed of Life!

ለመጪዎቹ በዓላት ከ13 ነጥብ 6 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለገበያ ይቀርባል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለቀጣዮቹ የትንሳኤ እና ዒድ ዓልፈጥር በዓላት ከ13 ነጥብ 6 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ስራ አስፈጻሚ መስከረም ባህሩ እንደገለጹት ÷ ለመጪዎቹ በዓላት የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ለዚህም ከሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና የፌዴራል ተቋማት ጋር የጋራ እቅድ ተዘጋጅቶ በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም በበዓላት ወቅት ይበልጥ ተፈላጊ ለሆኑ እና እጥረት በሚከሰትባቸው ምርቶች ላይ በየደረጃው ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ከምግብ ዘይት አቅርቦት ጋር ተያይዞ በመንግስት ከውጭ የሚገባ እና በሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች የተመረተ ዘይትን ለበዓላቱ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ከፊቤላ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሊትር ዘይት እና ከሸሙ ደግሞ 5 ሚሊየን ሊትር ዘይት ለክልሎች መደልደሉን ስራ አስፈጻሚዋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚገኘውን የምግብ ዘይትም አከፋፋዮች በፍጥነት አንስተው ከበዓላቱ በፊት ለክልሎች ተደራሽ እንዲያደርጉ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል፡

በሌላ በኩል በንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ከዚህ በፊት ከውጭ ገብቶ ያልተሰራጨ 1 ሚሊየን ሊትር ዘይት መኖሩን ጠቁመው ÷አሁን ላይም 5 ሚሊየን ሊትር ዘይት በመጓጓዝ ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በአጠቃላይም ከኮርፖሬሽኑ 6 ሚሊየን ሊትር እንዲሁም ከፊቤላና ሸሙ 7 ነጥብ 6 ሚሊየን በድምሩ ከ13 ነጥብ 6 ሚሊየ ሊትር በላይ ዘይት ለበዓላቱ ለገበያ ለማቅረብ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የዘይት ምርቱ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብተረሰቡ ተደራሽ እንዲሆንም በየደረጀው በሚገኙ የመንግስት አካላት አስፈላጊው ቁጥጥር ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.