Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዲጂታል የዳኝነት አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ ለማገዝ እና ይበልጥ ቀልጣፋ እና ፈጣን ፍትህ ለመስጠት የሚያስችል በዲጂታል የታገዘ የዳኝነት አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

በስምምነቱ መሰረትም ኢትዮ ቴሌኮም አስተማማኝ እና ደረጃውን የጠበቀ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት መዘርጋት ይጠበቅበታል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንደገለጹት÷ በተለይም አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት፣ የመጠባበቂያ ኔትወርክ እና የኔትወርክ ደኅንነት ያለው ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማዕከል ይገነባል፡፡

በተጨማሪም የኔትወርክ ኦፕሬሽን መቆጣጠሪያ ማዕከል እና ሌሎችንም ያካተተ መሰረተ ልማት የመዘርጋት ስርዓት እንደሚከናወን ገልፀዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት እንዳሉት÷ የመሰረተ ልማቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ በፌደራል ፍርድ ቤት የሚሰጠውን የዳኝነት አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ አስተማማኝ እና ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል፡፡

እንዲሁም ጊዜና ገንዘብን ለመቆጠብ በፍትህ ስርአት ግልፀኝነት ለማስፈን ብሎም ዜጎችን በፍትሕ ስርዓት ላይ እምነት እንዲኖራቸው ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

በቅድስት ተስፋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.