Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ባንክ በውኃ ሃብት አጠቃቀም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ ከዓለም ባንክ የውሃ ዘርፍ ዳይሬክተር ሳሮጅ ኩማር እና ልዑካን ቡድናቸው ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በሀገር አቀፍ የውኃ ሃብት አጠቃቀምና አስተዳደር ዙሪያ መምከራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡

በዚህም እስከ 10 ሚሊየን የሚደርሱ ኢትየጵያውያን የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እንዲኖራቸው ማድረግ መቻሉ ነው የተገለጸው፡፡

ኢትዮጵያ በገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ያላትን የውሃ ሃብት በማስተዳደር ሂደት ከድርቅ፣ ጦርነት፣ ጎርፍ አደጋና ከመሬት አቀማመጥ እንዲሁም ከማስፈጸም አቅም ውስንነት ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች መኖራቸው ተጠቅሷል፡፡

ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ÷ የዘርፉን ፖሊሲ ከመከለስና አዲስ ተቋማዊ መዋቅር ከማዘጋጀት ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የውሃ ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሳሮጅ ኩማር በበኩላቸው ÷ የዓለም ባንክ ዘርፉ በሚፈልጋቸው ስትራቴጅያዊ የድጋፍ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል፡፡

ለዚህም ባንኩ በአጽንኦት ከሚደግፋቸው ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደመሆኗ መጠን በልዩ ትኩረት እንደሚመለከቱትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.