“ጉዳይ ለማሥፈፀም ቢጫ ትኬት ቁረጡ” በማለት ሲያታልሉ የነበሩ 9 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)”ጉዳይ ለማሥፈፀም ቢጫ ትኬት ቁረጡ” በማለት በተለያዩ አካባቢዎች በተሽከርካሪ እየተንቀሳቀሱ የማታለል ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 9 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን የሚፈፅሙት የኢሚግሬሽን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ጉምሩክ ሠራተኛ እና የሥራ ኃላፊ በመምሰል መሆኑን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወንጀል የሚፈፅሙት በኢሚግሬሽን እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ጉዳይ ለማስፈፀም እንዲሁም በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጉምሩክ ከካርጎ ዕቃ ለማውጣት የሚመጡ ግለሰቦችን ለይተው እና ተከታትለው በመቅረብ መሆኑንም ፖሊስ አስታውቋል።
ከውጭ የገቡትን የግለሰቦችን ዕቃዎች አታለው ካስጫኑም በኋላ ይዘው እንደሚሰወሩ ፖሊስ ባደረገው የተጠናከረ ጥበቃ እና ክትትል መድረሱን ገልጿል፡፡
የምርመራ ሥራው መቀጠሉንም ፖሊስ ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ተክለ ሃይማኖት ሆስፒታል በተለምዶ ሶማሌ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተሰርቀው የተከማቹ 30 የተሽከርካሪ ስፖኪዮ መስታዎቶች ፣ 11 የተሽከርካሪ ቴፖች አናት እንዲሁም የተለያዩ የተሽከርካሪ ዕቃዎችን መያዙን ገልጿል፡፡
በዚሁ ጉዳይ የተጠረጠሩ ሶስት ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና ምርመራ ማካሄድ መጀመሩን ጠቁሟል፡፡