በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከ75 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ ለተከላ ዝግጁ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከ75 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ ለተከላ ዝግጁ መሆኑን የክልሉ ቡና ሻይ ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ገለፀ።
በክልሉ ካለው መሬት ከ550 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ ተናግረዋል።
ዘንድሮ ላይ ከ75 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ በመትከል ሽፋኑን ከዚህ በፊት ከነበረው በ30 ሺህ ሄክታር ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለፁት።
በሚያዚያና በግንቦት ወራት በሚደረገው ተከላ ከ66 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ከችግኝ ዝግጅት በተጨማሪ 600 ኩንታል የቡና ዘር መዘጋጀቱን ጠቅሰው÷181 ኩንታል በደቡብ ክልል እንዲሁም 50 ኩንታል በሲዳማ ክልል የሚሰራጭ እንደሆነ ተናግረዋል።
አርሶ አደሮችም ለዘንድሮ የቡና ችግኝ መትከያ የሚሆን መሬት ማዘጋጀታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በአለማየሁ መቃሳ