በሙስና ወንጀል የተከሰሱት የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ያለአግባብ የሲሚንቶ ግዢ በመፈፀም ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅም አውለዋል ተብለው በሙስና ወንጀል የተከሰሱ አራት የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ።
በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው ተከሳሾች 1ኛ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተቋም የኮንስትራክሽን እና ሎጅስቲክስ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ደሜ ፣ 2ኛ በተቋሙ የኮንስትራክሽን እና ሎጅስቲክስ ግዢ ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ አሸናፊ ተስፋዬ ፣ 3ኛ በተቋሙ የግዢ ባለሙያ ናቸው የተባሉ ቱጅባ ቀልቤሳ እና 4ኛ ተከሳሽ ሙስጠፋ ሙሳ ናቸው።
ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው፡፡
ተከሳሾቹ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የግዢ ፍላጎት ሳይኖረው ትዕዛዝ ባልተሰጠበት እና ከተቋሙ ዕውቅና ውጪ የግዢ ባለሙያ ሆነው ሲሰሩ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በ2013 እና 2014 ዓ.ም በተለያዩ ቀናቶች ለተቋሙ ነው በሚል ከሁለት ፋብሪካዎች የገዙትን 29 ሺህ 200 ኩንታል የሲሚንቶ ምርት ለግለሰቦች በመሸጥ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ሲል ዐቃቤ ህግ ታህሳስ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸውና በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ሶስት ምስክሮች አቅርቦ አሰምቷል።
የዐቃቤ ህግን የምስክሮችን ቃል ያዳመጠው ችሎቱ የምስክር ቃል መርምሮ ዛሬ በዋለው ችሎት ሁሉም ተከሳሾች በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ