በኦሮሚያ ክልል ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ችግኝ እየተዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊና የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ኤሊያስ ከድር ÷ በክልሉ ሁሉም ዞኖች ለቀጣዩ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚውል ችግኝ የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ ነው፡፡
በዚህ መሰረት ለመጪው ክረምት በክልል ደረጃ 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ችግኝ ለማዘጋጀት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ከሚዘጋጀው 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ችግኝ ውስጥ 1 ነጥብ 49 ቢሊየኑን ለመትከል መታቀዱን ጠቁመዋል።
እስካሁን በተከናወነ ስራም 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኝ ለቆጠራ መድረሱን ጠቁመው÷ ከተዘጋጁ የችግኝ አይነቶች ውስጥም ለደን ልማት የሚውሉ፣ የፍራፍሬ ዝርያዎች፣ የቀርከሃ እና ሌሎች መካተታቸውን አንስተዋል፡፡
ከችግኝ ዝግጅቱ ጎን ለጎንም የመትከያ ቦታ የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በቀጣዩ ክረምት ችግኞቹን ከ1 ነጥበ 3 ሚሊየን ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ ለመትከል መታቀዱንም ነው ያስረዱት፡፡
በመላኩ ገድፍ