የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ሥራ በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ወቅት የተጀመረ ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሁን ወደ ተግባር የገባው የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ሥራ በሁሉም ክልሎች ውስጥ በተመሳሳይ ወቅት የተጀመረ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በመከላከያ ሠራዊት የተካሄደው ሪፎርም በመሣሪያ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል እንዲሁም አስፈላጊ በሆኑ ሌሎች መንገዶች ሁሉ ማጠናከር ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ይህም እንደ ሀገር ተደቅኖብን የነበረውን የኅልውና አደጋ በዘላቂነት መቀልበስ ያስቻለም መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ከክልል ልዩ ኃይሎች ማደራጀት ጋር በተያያዘ የተጀመረው ሥራ በጥናትና በቅደመ ዝግጅት ደረጃ ቆየት ብሎ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ሀገር ተደቅኖ የነበረው የኅልውና አደጋ መቀልበስ አስፈላጊ በመሆኑ እና በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ የሰላም መደፍረሶች ዘላቂ መፍትሄ እስከሚያገኙ ድረስ በጥናቱ ላይ የተመለከቱ አቅጣጫዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ አድርጎ መቆየቱን ነው ያነሱት።
ይሁን እንጅ አሁን አንድ ጠንካራ እና የተማከለ ሰራዊት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት፥ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ብሔራዊ እና የመጨረሻ የኅልውና ምሽግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ በብዙ ቀጣናዊ ትኩሳት ለተከበበ ሀገር ያለ ጠንካራ መከላከያ ሠራዊት ጠንካራ ሀገርን መገንባት አይቻልምም ብለዋል፡፡
ለዚህም ሲባል መከላከያ ሠራዊትን በአግባቡ ማደራጀት ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የማደራጀት እና ሠራዊቱን የማጠናከር ሥራውን በጥናት ላይ የተመሰረተ መሆኑን በመጥቀስም፥ ጥናቱን ተከትሎ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የክልል ልዩ ኃይሎች በተለያዩ መዋቅሮች እንዲደራጁ የሚያስችላቸው ተግባራዊ እርምጃ መጀመሩን አስታውሰዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በመግለጫቸው ከተለያየ አቅጣጫ ሲሰነዘሩ የነበሩ ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ የጣሉ ክስተቶችን ለመመለስ እና ክብርን ለማስጠበቅ ልዩ ኃይሎች በመስዋዕትነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን በማውሳት ለዚህም መንግሥት ከፍተኛ ምስጋና አለው ብለዋል።
አሁን በተጀመረው የመልሶ ማደራጀት ሥራም ምርጫ ተጠብቆላቸው እና ፍላጎታቸው ተከብሮላቸው መንግሥት አማራጮችን አስቀምጦ የመልሶ ማደራጀት ሥራው እንደሚከናወን ነው የገለጹት።
ልዩ ኃይሎች መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል የመጀመሪያው አማራጭ መሆኑን እና ሀገራዊ ጥሪ መሆኑንም ጭምር ነው መንግስት የገለጸው፡፡
እንዲሁም በክልል የጸጥታ ተቋማት እና ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ የሚሉት ሌሎች አማራጮች እንዳሉ አንስተው፥ ወደ ሲቪል ለሚመለሱ መቋቋሚያ እና አስፈላጊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉንም አብራርተዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች በመረጃ እጦት እና የመርሐ ግብሩን ዓላማ በአግባቡ ባለመገንዘብ ያጋጠሙ ችግሮች መኖራቸው ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም በመግባባት ብቻ የሚከናወን ሥራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
መርሐ ግብሩ ትጥቅን ከማስፈታት ጋር ግንኙነት እንደሌለው መረዳት ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ሂደቱም በጥንቃቄ እንደሚከናወን እና የጸጥታ ስጋት ላለባቸው አካባቢዎችም መከላከያ ሠራዊት ስምሪት ተሰጥቶት ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከህወሓት ጋር በተያያዘም በተደረሰው እና በተቀመጠው ስምምነት መሠረት ሥራዎች እየተከናወነ ስለመሆናቸው ነው የገለጹት፡፡
የልዩ ኃይሎች መልሶ መቋቋምን በተመለከተ የሚነዙ ሐሰተኛ የጥፋት ረጃዎችን መስማት ተገቢ እንዳልሆነ መክረዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!