የቀድሞ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታ (ዶ/ር) ፍርድ ቤት ቀረቡ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታ (ዶ/ር) ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ተጠርጣሪው በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ነው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረቡት።
በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ያለመከሰስ መብታቸው በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተነሳው የቀድሞ የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታ ( ዶ/ር) ላይ በተከፈተ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
ተጠርጣሪው በዩኒቨርሲቲው ኃላፊ በነበሩበት ወቅት የግዢ መመሪያን ባልተከተለ መንገድ የንብረት ግዢ ማከናወን፣ ህግን ያልተከተለ የስራ ተቋራጭ ውል መፈጸም እና ወደ ስራ ማስገባት እንዲሁም ያልተገባ ጥቅም በማግኘት የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ መጀመሩን ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።
በዚህም መነሻ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ያብረራው መርማሪ ፖሊስ÷ ቀሪ የሰነድና የሰው ምስክር ቃል ለመቀበልና ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።
ተጠርጣሪው በበኩላቸው÷ ምንም ወንጀል አልፈጸምኩም ሲሉ በመከራከር የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።
መርማሪ ፖሊስ በዋስ ቢወጡ ማስረጃ ሊያሸሹብኝ፤ ምስክር ሊያባብሉብኝ ይችላሉ በማለት ስጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄያቸውን በመቃወም ተከራክሯል።
የምርመራ መዝገቡን የተመለከተው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የተጠርጣሪውን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ በማድረግ ተጨማሪ ምርመራ ማስፈለጉን በማመን ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ