Fana: At a Speed of Life!

ልዩ ኃይልን በአዲስ መልክ ለማደራጀት በተዘጋጀው ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልል ልዩ ኃይልን በአዲስ መልክ ለማደራጀት በተዘጋጀው የማስፈፀሚያ ዕቅድ ላይ በአዲስ አበባ ውይይት ተካሄደ፡፡

ውይይቱ የተካሄደው÷ የሀገር መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮች እና የክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት ነው፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል ኤታማጆር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ÷ የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች በየክልላቸው የደረሱበትን መግባባት አድንቀዋል፡፡

የሚነሱ ጥያቄዎችን በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ደረጃ መሰረት በውይይት መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ወደ መከላከያ ሠራዊት የሚቀላቀሉ የክልል ልዩ ኃይል አባላት ጥቅማቸው ተጠብቆ በክብር እንደሚቀበሏቸው ገልፀዋል፡፡

በጡረታና በቦርድ በክብር የሚሰናበቱ አባላትም መብታቸው እንደሚጠበቅላቸው ነው ያረጋገጡት፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል÷ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ በፌደራል ማረሚያ ቤት እና በክልል መደበኛ ፖሊስ በተቀመጠው መስፈርት በልዩ ኃይሎቹ አባላት ፍላጎት ወደ ተቋማቱ መቀላቀል እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡

የልዩ ኃይል አባላቱን በሀገር መከላከያና በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተቋም ውስጥ ከነሙሉ ጥቅምና ክብራቸው እንደሚቀበሉም አረጋግጠዋል፡፡

አዲሱ አደረጃጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጠናከረ የፖሊስ አገልግሎትን ለሕብረተሰቡ ለመስጠት ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በተዘጋጀው ስታንዳርድ መሠረት ሬንጀር የደንብ ልብስ የሚጠቀሙት የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ብቻ መሆናቸው አስረድተዋል፡፡

የክልል መደበኛ ፖሊስ ወጥ የሥራ የደንብ ልብስ ይለብሳል ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጥሩነህ እንዳሉት÷ በማስፈፀሚያ ዕቅዱ የክልል ልዩ ኃይል በአዲስ መልክ እንዲደራጅ የተወሰነው ከለውጡ በፊት ነው፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ስለነበሩ ተግባራዊነቱ መዘግየቱን አንስተዋል፡፡

አደረጃጀቱም ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያገናዘበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ ሁለቱ የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮች እና የክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች የተጀመረውን አደረጃጀት በተቀመጠው ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ መስማማታቸው ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.