ከመዲናዋ ነዋሪዎች ለህዳሴ ግደብ 518 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 9 ወራት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 518 ሚሊየን ብር ድጋፍ መሰብሰቡን በአዲስ አበባ የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባባሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስታውቋል።
የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 12ኛ ዓመት በማስመልከት ዛሬ በየካ ክፍለ ከተማ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምስክር ነጋሽ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ለግድቡ ግንባታ ስኬት የመዲናዋ ነዋሪዎች ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ከመዲናዋ ነዋሪዎች 4 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ከመዲናዋ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች 685 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 518 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
የክፍለ ከተማው ምክትል ስራ አስፈጻሚ ፀሐይ ኪባሞ በበኩላቸው÷ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠ ጀምሮ የህብረተሰቡ ድጋፍና ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደቀጠለ መግለጻቸውን የየካ ክ/ከተማ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡።
የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በክፍለ ከተማው ህብረተሰብ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከነዋሪዎች ከ40 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።