Fana: At a Speed of Life!

ትንሣዔ – የድል ቀን !

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዐቢይ ጾም የመጨረሻው ሣምንት ሰሙነ ሕማማት (የሕማማት ሣምንት) ይባላል፡፡

“ሰሙን” ሳምንት ማለት ሲሆን÷ ሕማማት ደግሞ “ሐመ” ታመመ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ መታመም ፤ መሠቃየት ማለት ነው፡፡

የሁለቱ ቃል ጥምረት የኢየሱስ ክርስቶስ ሕመሙና ሞቱ የሚዘከርበት ሣምንት መሆኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ዋና ኃላፊ መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል ሰሙነ ሕማማት የኦሪት ዘመን ምሳሌ ስለመሆኑ አንስተው፥ በዘመነ ኦሪት (አዳም ከገነት ከተባረረበት ጀምሮ ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም እስከተወለደበት ዘመን) የሰው ልጅ የጽድቅ ሥራው ለመንግሥተ ሰማያት የማያበቃው ነበር ይላሉ፡፡

ይልቁንም ነቢዩ ‘’ጽድቃችን የመርገም ጨርቅ ሆነ’’ (ኢሳ 64:6) እንዳለ፤ የአዳም ዘር በሙሉ እስከ ዕለተ ዐርብ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ የሰው ልጅን እስካዳነበት ድረስ የሰው ልጆች በዲያብሎስ በባርነት ሥር ነበሩና ሰሙነ ሕማማትም የዘመነ ፍዳ ምሳሌ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል” (ኢሳ.53:4) እንዳለ፤ በክርስቶስ ክቡር ደም የዳነ ክርስቲያን መድኃኔዓለም ክርስቶስ የተቀበለው መከራና ሞት ስለ እኔ ኃጢአት ነው ብሎ በማመን በጸሎት ፤ በጾምና በስግደት ሆኖ ክብርን ሁሉ ለአምላኩ የሚሰጥበት ወቅት በመሆኑ ሰሙነ ሕማማት ለአማኞች የቅድስና የመንፈሳዊ ሀብት መገኛ ነው ይላሉ፡፡

ጸሎተ ሐሙስ!

በሰሙነ ሕማማት 4ኛው ቀን “ጸሎተ ሐሙስ” “ትእዛዘ ሐሙስ” “ሥርዓተ ሐሙስ” ወዘተረፈ በመባል እንደሚከበር መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ (ዶ/ር) አብራርተዋል።

“ጸሎተ ሐሙስ” መባሉ ጌታ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 17 የሚገኘውን ረዥም ጸሎት የጸለየበት በመሆኑ ነው ብለዋል ኃላፊው፡፡

“ትእዛዘ ሐሙስ” መባሉም “እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና” (ዮሐ.13:15) እና “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ” (ዮሐ.15:34) ብሎ አዲስ ትእዛዛትን የሰጠበት ቀን ስለሆነ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

“ሥርዓተ ሐሙስ” መባሉም ሥርዓተ ሕጽበትን (ትሕትናን) እና ሥርዓተ ቁርባንን የመሠረተበትና ያስተማረበት በመሆኑ ነው ብለዋል ኃላፊው፡፡

ለአማኞች ሕይወት የቅድስና የሕዳሴ ቀን መሆኑን እንዲሁም ኃጢአትን የሚያስተሠርይ ፤ ርኩሰትን የሚቀድስ ያደፈ ማንነትን የሚለውጥ ቅዱስ ቁርባን የተሰጠበት ስለመሆኑም ነው የተናገሩት፡፡

ምዕመኑ መከባበርና አንዱ ለአንዱ መልካም ማድረግን የሚማርበት ዐውድ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ክርስቲያኖች በዐለ ትንሣኤን የሚያከብሩበት ዐውድ ፤ የሚገልጹበት ሃይማኖታዊ መስተጋብሮች እጅግ ብዙ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ሁለቱን አንስተው ትንሣኤ “የድልና የሰላም” በዓል ነው ይላሉ፡፡

ካህኑና ምዕመኑ እየተቀባበሉ በቤተ ክርስቲያን የሚታወጀው የድልና የሰላም አዋጅ÷ “ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ በታላቅ ኀይልና ሥልጣን፡፡ ሰይጣንን አሰረው። አዳምን ነጻ አወጣው። ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት ከዛሬ ጀምሮ ሰላምና ደስታ ሆነ” በማለት ክርስቲያኖች ሰላምን ያውጃሉ። በግዞት ፤ በጎዳና ወድቀው ያሉትን ያስባሉ። ያላቸውን ያካፍላሉ ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ትንሣዔ!

የፊታችን እሑድ ሚያዝያ 8 ቀን 2015 ዓ.ም በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ የትንሣዔ በዓል ይከበራል፡፡

ትንሣኤ ሥርወ ቃሉ “ተንሥአ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን÷ ፊደላዊ እና መንፈሳዊ ትርጓሜዎች አሉት፡፡

መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ (ዶ/ር) ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ፊደላዊ ትርጉሙ “ተንሥአ” ተነሣ፣ መነሣት፣ መንቃት፣ አነሣሥ ማለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንፈሳዊ ትርጉሙም በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በአምስት የተለያዩ የትርጉም ዓይነቶች ተከፍሎ እደሚተረጎም ነው ያስረዱት፡፡

እነሱም፦

1. “ትንሣኤ” ማለት ሕሊና ወይም ንቃወ ሕሊና ፤ ተዘክሮተ እግዚአብሔር ማለት ነው።

2. “ትንሣኤ” ልቡና ሲሆን የታደሰ ሕይወትን መኖር ወይንም በታደሰ ሕይወት መመላለስ ማለት ነው፡፡

3. “ትንሣኤ” የሙታን በሥጋ መነሣት ወይም “ትንሣኤ ዘለኃሣር” ነው። ነገር ግን ይኽ የኃጢአን ትንሣኤ ዘለዓለማዊ ሞት ይከተለዋል።

4. «ትንሣኤ» ክርስቶስ በኃይልና በሥልጣን ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ነው፡፡ “አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል” (1.ቆሮ.15:20) እንዲል።

5. “ትንሣኤ” “ትንሣኤ ዘጉባኤ” ነው። ይኽም የባሕርይ አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስን “ትንሣኤ” መሠረት ያደረገ ሲሆን÷ ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ሁሉ እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኩነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ይሆናል፡፡

በሌላ መልኩ የትንሣኤ በዓልን በምሥጢርም በይዘትም የሚመሳሰለው፣ ጥላውና ምሳሌው የሆነው “ፋሲካ” የሚለው ሥያሜ መሆኑን መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ቃለጽድቅ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

“ፋሲካ” ማለት በአረማይክ “ፓስኻ”፣ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ፐሳኽ” በጽርእ (ግሪክኛ) “ፓስቃ” እንደሚባል እና ወደ ግእዝና ዐማርኛ ቋንቋ ሲመለስም÷ ፍሥሕ፣ ዕድወት (ማዕዶት)፣ በዓለ ናእት (የቂጣ በዓል)፣ እየተቸኮለ የሚበላ መሥዋዕት፣ መሻገር፣ መሸጋገር ማለት ነው ይላሉ፡፡

ፋሲካ፥ እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የባርነት ቀንበር ወደ ነፃነት የተላለፉበት፣ ከከባድ ሀዘን ወደ ፍጹም ደስታ፣ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር፡፡ በዚህ ኦሪታዊ ምሳሌ በዓል አሁን አማናዊው በዓለ ትንሣኤ እንደተተካበት ያስረዳሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ፋሲካ በዘመነ ሐዲስ እስራኤል ዘነፍስ የሆኑት ክርስቲያኖች ትንሣኤውን የሚያከብሩበት ዕለት ሆኖ በክርስቶስ ትንሣኤ÷ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፤ ከኃሣር፣ ከውርደት ወደ ክብር፤ ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት፤ ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ ሐዲስ ማንነት የተሻገሩበት ታላቅ መንፈሳዊ የነፃነት በዓል ነው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል ነስቶ፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በሥልጣኑ የተነሣው ጥንተ ትንሣኤው መጋቢት 29 ቀን 34 ዓ.ም እንደሆነ ታሪከ ቤተ ክርስቲያን ያስረዳል ይላሉ፡፡

የበረከት ፤ የመተሳሰብ ፤ የርኅራኄ በዐል እንዲሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ዋና ኃላፊ መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ (ዶ/ር) መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.