የድንበር አካባቢ ትብብርን ማሳደግ ቀጠናዊ ውህደትን እውን ለማድረግ ይረዳል – አቶ አሕመድ ሺዴ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የድንበር አካባቢ ትብብርን ማሳደግ ቀጣናዊ ውህደትን እውን ለማድረግ እንደሚረዳ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሺዴ ገለጹ።
አቶ አህመድ ሺዴ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) የፀደይ ወቅት ስብስባ ጎን ለጎን በተካሄደው 16ኛው የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብስባ ላይ ተሳትፈዋል።
በዚህ ወቅትም የድንበር አካባቢ ትብብር ማደግ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ቀጣናውን ለማስተሳሰር የያዛቸውን ሕልሞች እውን ለማድረግ እንደሚረዳ ገልጸዋል።
በቀጣናው የሚስተዋሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ለመመከት የኢኒሼቲቩ አባላትና አጋር አካላት የተቀናጀ ጥረት ዒያደርጉ እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።
ተሳታፊዎቹም የተቀናጀ ድንበር ተሻጋሪ የደህንነት እና የመሰረት ልማት ሊኖር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ኢኒሼቲቭ በፈረንጆቹ 2019 የተቋቋመ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያና ኤርትራ የኢኒሼቲቩ አባል ሀገራት ናቸው።