ህፃን አፍኖ በመውሰድ ክፍያ የጠየቀው ግለሰብ እና ግብረ አበሮቹ በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የአምስት አመቱን ህፃን አፍኖ በመውሰድ የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ክፍያ የጠየቀው ግለሰብና ግብረ አበሮቹ በቁጥርር ስር ውለው ምርመራ መጀመሩ ተገለፀ፡፡
በህፃኑ እገታ ዋና ወንጀል ፈፃሚ የሆነው አማኑኤል ተክላይ የተባለው ግለሰብ ቤተሰባዊ ጉዳይን ምክንያት በማድረግ የ5ዓመቱን ህፃን ናታኒ ጎይቶምን ሚያዝያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው አለም ባንክ ስድስት ጎጆ ከሚባል አካባቢ ከሚገኘው የህፃኑ ወላጆች ቤት አፍኖ በመውሰድ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ካልተከፈለው ልጁን እንደሚገድለው መዛቱ ተገልጿል፡፡
የህፃኑ መታገት መረጃው የደረሰው አዲስ አበባ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ጋር በጥምረት ምርመራና ክትትል ማድረጉ ተመላክቷል፡፡
በዚህም ወንጀል ፈፃሚዎቹ ከአርባ ምንጭ – ሀዋሳ ከዚያም አዳማ ከተማ እየተዘዋወሩ አድራሻቸውን ለማጥፋት ጥረት ቢያደርጉም በተደረገ ጠንካራ ክትትል እና ምርመራ ሚያዝያ 14 ቀን 2015 ዓ.ም ቢሾፍቱ ከተማ ሸማኔ ሜዳ አካባቢ ህፃን ናታኒም ጎይቶም ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስበት ማግኘታቸው ታውቋል፡፡
በዚህ የህፃን አፈና የወንጀል ድርጊት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እጃቸው ያለበትን ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ህግ ፊት ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡