ሩሲያ ለቻይና የማደርገውን የጋዝ አቅርቦት አሳድጋለሁ አለች
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ለቻይና የምታደርገውን የጋዝ አቅርቦትን አሳድጋለሁ ማለቷ ተሰምቷል፡፡
ሩሲያ ከቤጂንግ ጋር የኃይል ትብብሯን እያሳደገች ከመምጠቷ ጋር ተያይዞ በዚህ ዓመት ወደ ቻይና የምትልከውን የተፈጥሮ ጋዝ በ50 በመቶ ታሳድጋለች ሲሉ የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ኖቫክ ተናግረዋል።
ኖቫክ ከሩሲያ-1 የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው ባለፈው ዓመት ሞስኮ 15 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ ለቻይና ማቅረቧን እና በዚህ ዓመት 22 ኪዩቢክ ሜትር ለማድረስ ቃል መግባቷን ያስታወቁት።
በተጨማሪም በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በሳይቤሪያ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር በኩል የምታቀርበው ጋዝ በዓመት 38 ኪዩቢክ ሜትር ይደርሳልም ብለዋል የሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር።
ቻይና በአሁኑ ጊዜ አብዛኛውን የሩሲያ ጋዝ የምታገኘው በዚህ ትልቅ የጋዝ መስመር በኩል ሲሆን ፥ ይህም የምስራቃዊ መስመር ተብሎ የሚጠራው ክፍል ነው።
የሩሲያ ጋዝን ለቻይና ለማቅረብ የመጀመሪያው የጋዝ መስመር በመሆን በፈረንጆቹ በታህሳስ 2019 በከፊል ማቅረብ መጀመሩን የአር ቲ ዘገባ አመላክቷል።
የሳይቤሪያ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር በሩሲያ ውስጥ 3 ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ፥ በቻይና ውስጥ ደግሞ እስከ 5 ሺህ 111 ኪሎ ሜትር የሚደርስ መሆኑም ተገልጿል።
የሳይቤሪያ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር በፈረንጆቹ ግንቦት 2014 በሩሲያ ጋዝፕሮም እና በቻይና ናሽናል ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን መካከል የተደረሰ የ30 ዓመት የ400 ቢሊየን ዶላር ስምምነት አካል እንደሆነም ተነግሯል።