
የአውሮፓ ህብረት በካርቦን ልቀት ላይ የ2030 የአየር ንብረት ግቦችን አጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት በካርቦን ልቀት ላይ የ2030 የአየር ንብረት ግቦችን አጽድቋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ህብረቱ የባህር ትራንስፖርት እና የአቪዬሽን ኢንዱስትሪን ጨምሮ በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚለቀቀውን በካይ ጋዝን ለመቀነስ የሚያስችሉ አምስት አዳዲስ ህጎችን አጽድቋል።
ህጉ የአውሮፓ ህብረት ዋና የአየር ንብረት እርምጃ የሆነውን “55ትን የሚመጥን” የተሰኘውን በ1990 ከተቀመጠው ደረጃ አንፃር በ2030 በተሻለ በካይ ጋዝ ልቀትን ቢያንስ በ55 በመቶ ለመቀነስ ያለመ ማዕቀፍ አካል ነው።
“በካዮች ይከፍላሉ” በሚለው መርህ ላይ የተመሰረተው የአውሮፓ ህብረት የካርበን ገበያ ÷ ለሀይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች፣ ለሃይል አመንጪዎች እና የአቪዬሽን ዘርፍ ለሚለቁት በካይ ጋዝ ክፍያ ይፈፅማል።
ሆኖም በአዲሱ የልቀት ንግድ ሥርዓት ህግ መሰረት እንደ ኃይል፣ ብረት፣ ወረቀት እና ዘይት ኢንዱስትሪዎች ያሉ ዘርፎች የበካይ ጋዝ ልቀትን ከ2005 ስምምነት አንፃር በ62 በመቶ መቀነስ እንደሚገባቸው የሲ ጂ ቲ ኤን ዘገባ አመላክቷል።
በአቪዬሽን ዘርፍ ያለው የነፃ ልቀት የክፍያ ሁኔታም ከፈረንጆቹ 2026 ጀምሮ ቀስ በቀስ እንዲያበቃ ይደረጋልም ነው የተባለው።
ከባህር ማጓጓዣ የሚመነጭ የበካይ ጋዝ ልቀትም ለመጀመሪያ ጊዜ በልቀት ንግድ ሥርዓት ውስጥ እንደሚካተት ተገልጿል፡፡
ለባህር ማጓጓዣ ኩባንያዎች ከ2024 ጀምሮ ለተረጋገጠ ልቀት 40 በመቶ፣ ከ2025 ጀምሮ 70 በመቶ እና ከ2026 ጀምሮ ደግሞ 100 በመቶ ክፍያ የማስረከብ ግዴታዎች ቀስ በቀስ እንደሚተዋወቅ ተጠቁሟል።
ለህንፃዎች፣ ለመንገድ ትራንስፖርት እና ለአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች አዲስ የተለየ የልቀት ግብይት ስርዓት ተፈጥሯል ነው የተባለው።
ይህም በነዚህ ዘርፎች ወጪ ቆጣቢ የልቀት ቅነሳን ለማረጋገጥ ሲሆን ፥ እስካሁን ድረስ አካባቢን ከበካይ ጋዝ ልቀት ነፃ ማድረግን አስቸጋሪ አድርጎታል።
አዲሱ አሰራርም ከፈረንጆቹ 2027 ጀምሮ ለህንፃዎች፣ ለመንገድ ትራንስፖርት እና ለተጨማሪ ዘርፎች ነዳጅ በሚያቀርቡ አከፋፋዮች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።
አዲሱ አሰራር ሊጀመር በቀረበበት ወቅት የነዳጅ እና ጋዝ ዋጋ በተለየ ሁኔታ ከፍ የሚል ከሆነ እስከ 2028 ድረስ ለማራዘም አሰራር መዘርጋቱም ተጠቁሟል።