በእነ ሲሳይ አውግቸው (ረ/ፕ) ላይ የ10 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ ሕገ መግሥቱን በኃይል ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብለው በተጠረጠሩት በእነ ሲሳይ አውግቸው (ረ/ፕ) ላይ የ10 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።
እንዲሁም በዚሁ መዝገብ ተካተው የነበሩት የባልደራስ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አማሃ ዳኘው ከተጠረጠሩበት የወንጀል ተሳትፎና ካሉበት ዕድሜ አኳያ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መስጠት ተገቢ ባለመሆኑ በ30 ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል፡፡
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሲሳይ አውግቸው (ረ/ፕ) ጨምሮ በአራት ተጠርጣሪዎች ላይ መርማሪ ፖሊስ የሠራውን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ተጨማሪ ምርመራ ማከናወን ያስፈልጋል በማለት የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
መርማሪ ፖሊስ ከትናንት በስቲያ በነበረ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ ሲሳይ አውግቸው (ረ/ፕ)፣ ማዕረጉ ቢያበይን (ፕ/ር)፣ ሰለሞን ልመንህ እና ሄኖክ አዲስን በሚመለከት ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ በማሰብ በአማራ ክልል ሁከትና ብጥብጥ አመፅ በማስነሳት በንብረትና በሰው ላይ በደረሰ ጉዳት ተሳትፎ እንዳላቸው የሚገልፁ የሠነድ ማስረጃዎችን ማግኘቱን ገልጾ ነበር።
በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ ለበጎ አድራጎት ዕርዳታ በሚል ሰበብ አባላት መልምለው በአጣዬ አካባቢ ስልጠና ሲሰጡ እንደነበር የተገኘው ማስረጃ በግልፅ ያሳያል ሲል ለችሎቱ አስረድቷል።
የተለያዩ የገንዘብ ዝውውሮችን ለማጣራት ለባንኮች ደብዳቤ መጠየቁን እና በተጠርጣሪዎች ዕጅ የተገኘ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን፣ የተያዙ ቦንቦችንና የጦር መሳሪያዎችን እንዲሁም በሰለሞን ልመንህ ዕጅ የተገኙ የበርካታ ወጣቶች መታወቂያዎችና ሠነዶችን ሕጋዊነት የማጣራት ሥራ እየሠራ መሆኑን በመግለጽ ቀሪ የምርመራ ሥራዎችን አከናወኖ ለማቅረብ 14 ቀን እንዲሰጠው መጠየቁ ይታወሳል።
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ለፖሊስ ከዚህ በፊት የተሰጠው ጊዜ በቂ መሆኑን ጠቅሰው ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ሊሰጥ አይገባም በማለት የተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት እንዲፈቀድ ጠይቀው ነበር፡፡
መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ማስረጃ ሊያሸሹ ይችላሉ ሲል ስጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሞ መከራከሩ ይታወቃል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ዳኛ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በርካታ ማስረጃ መሰብሰቡን ከምርመራ መዝገቡ መመልከቱን አብራርቷል።
በዚህም መሰረት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲል ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!