በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩ ምርምሮች በአካባቢያቸው የሚገኙ ችግሮችን መቅረፍ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ምርምሮች በአከባቢያቸው የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
9ኛው ዓመታዊ የምርምር ኮንፈረንስ ”ጥራት ያለው ምርምር ለተቋማዊ ልህቀት” በሚል መሪ ቃል በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
በኮንፈረንሱ ከሀገር ውስጥና ከውጪ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተወጣጡ ተመራማሪዎች ዓመታዊ የምርምር ጥናታቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የምርምር ኮንፈረንሱ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን÷ በዚህም 36 የሚደርሱ የምርምር ስረዎች እንደሚቀርቡ ተመላክቷል፡፡
በዚህ መሰረትም 16ቱ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና 20 ምርምሮች ደግሞ በተለያዩ ተቋማት እንደሚቀርቡ ነው የተገለፀው።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ ምርምሮች በአከባቢው የሚገኙ ችግሮችን ከመቅረፍ ባለፈ ዓለም አቀፋዊ ጠቀሜታ መስጠት እንዳለባቸው የአርማወር ሀንሰን የምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) ተናግረዋል።
አሁን ላይ ሴቶች በምርምር ላይ የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው÷ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በጀማል ከዲሮ