Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በንፁህ ውሃ አቅርቦት እና በንፅህና አጠባበቅ ላይ በኔዘርላንድስ በተካሄደው መድረክ ተሳተፈች  

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በንፁህ ውሃ አቅርቦት እና በንፅህና አጠባበቅ ላይ በኔዘርላንድስ ሄግ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ተሳትፋለች።

 

መድረኩ ከ800 በላይ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሲሆን፥ በዘርፉ ላይ ባሉ መሰረታዊ አጀንዳዎች ላይ ሲመክር ሰንብቶ ተጠናቋል፡፡

 

በምክክር መድረኩ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰውን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትንና ድርጅቶችን የወከሉ ከ25 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

 

የጉባኤው ዋና ዓላማ በፈረንጆቹ ከማርች 22 እስከ 24 በአሜሪካ ኒውዮርክ ሲካሄድ የሰነበተውን የተመድ የውኃ ጉባኤ ማጣቃለያ መርሐ ግብር እና የዘላቂ ልማት ግቦች ቀሪ ስራዎች ላይ መነሻ በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች እንዲኖሩ ያለመ ነው፡፡

 

በኢትዮጵያ ልዑካን በኩል በመድረኩ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን ኢትዮጵያ ካላት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባሻገር ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዞ በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በተከታታይ ዓመታት የቀጠለው የድርቅ አደጋ፣ የዋና ዋና የልማት ፕሮግሞች ማስፈጸሚያ የሀብት እጥረት፣ የማስፈጸም አቅም ውስንነቶችና በዓለም አቀፍ ገበያ እየተከሰተ ያለው የዋጋ ንረትን ጨምሮ እያጋጠሙ ስላሉ ተግዳሮቶች ቀርበዋል።

 

ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ተግዳሮቶች ቢያጋጥማትም በመንግስት በኩል የለጋሽ ድርጅቶችን ድጋፍ ከመጠቀም ባሻገር የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በቅንጅት እንዲሰሩ በማድረግ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በንፅህና አጠባበቅ ላይ ውጤታማ ስራ እንዳከናወነች ልዑኩ አቅርቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.