ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ኢኖቬሽን ዲጂታል ጉባኤ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ኢኖቬሽን ዲጂታል ጉባኤ ሰኔ 7 እና 8 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ጉባኤው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኤክስቴንሽያ ሊሚትድ ተቋም ጋር በትብብር እንደሚዘጋጅ የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።
ኢትዮጵያ ጉባኤውን በየዓመቱ እያካሄደች እንደምትገኝና ዘንድሮም በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/) ገልጸዋል።
በጉባኤው ከዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር የተያያዙ ርዕሰ ጉዳዮች ቀርበው እንደሚመከርባቸውና በርካታ ተያያዥ ሁነቶች እንደሚኖሩም ነው የገለጹት።
ጉባኤው ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ስኬት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ያሉት ሚኒስትሩ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችና ምሁራን እንዲገናኙ፣ በስራ እንዲተሳሰሩ፣ ልምድ እንዲጋሩ እና ሃሳብ እንዲለዋወጡ ያስችላልም ነው ያሉት።
ጉባኤው የኢትዮጵያን የመስህብ ሃብቶች ለጎብኚዎች በማስተዋወቅ ለቱሪዝም ዘርፉ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አንስተዋል።
በተጨማሪም በመላ ኢትዮጵያ በተለይም በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነት፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታና የብሮድባንድ አገልግሎት መስፋፋት፣ የዲጂታል ኢንቨስትመንትና ሃብት ፈጠራና የኢንተርኔት አገልግሎት ስርጭትና አስተዳደር ውይይቱ ከሚካሄድባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል መሆናቸው ተመላክቷል።
በውይይቱ ከ300 በላይ ከተለያዩ የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት የሚመጡ ሚኒስትሮች፣ የዘርፉ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ በዲጂታላይዜሽንና የኢኖቬሽን መስኮች ስራና ሃብት የፈጠሩ ኢንተርፕራይዞች ፣ በዘርፉ የተሰማሩ ታዋቂ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችና ባለሙያዎች ይሳተፋሉ ተብሏል።