ኢትዮጵያና ቻይና ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ቻይና ዘርፈ ብዙ ትብብራቸውን በማሳደግ ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማምተዋል፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ በኢትዮጵያ ባደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ መሠረተ ልማት፣ የኃይል አቅርቦትና ትራንስፖርት እንዲሁም በኢ-ኮሜርስ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎትና በአረንጓዴ ኃይል ልማት ላይ ያለውን ትብብር ለማጠናከር መክረዋል፡፡
ውይይቶቹን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባወጡት የጋራ መግለጫ÷ በቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ላይ የተላለፉ ውሳኔዎችን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ቻይና ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን እንደ ተሞክሮ በመውሰድ የቻይና-አፍሪካ የጋራ ማሕበረሰብን ለመገንባትና ሁሉን አቀፍ ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማምተዋል፡፡
በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ የተካሄደው የቻይና-አፍሪካ የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ ሀገራቱን በባህልና ኪነጥበብ ይበልጥ ለማቀራረብ የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡
ቻይና በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ሀገራዊ የልማት ሥራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን በማድነቅ ለኢትዮጵያ የእድገት ጉዞ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጣለች፡፡
ሁለቱ ሀገራት በልማት ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎች ያላቸውን ትብብር በማሳደግ እንዲሁም የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት ልምዶቻቸውን በመለዋወጥ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአንድ ቻይና መርህን እና የቻይናን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት እንደምታከብር በመግለጽ፥ የቻይና መንግሥት ሀገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ አረጋግጣለች፡፡
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም መረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ቻይና እያደረገች ያለውን ድጋፍ ማድነቋን የጋራ መግለጫው አውስቷል፡፡
ቻይና በበኩሏ የአፍሪካ ሀገራት ቀጣናዊ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርባለች፡፡
በተለይም የባሕር በር ተደራሽነትን በማረጋገጥና ሎጂስቲክስን በማሳደግ እንዲሁም አንድነታቸውን በማጠናከር አህጉራዊ ሰላምን፣ መረጋጋትንና ብልፅግናን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ አስገንዝባለች፡፡
ሁለቱ ሀገራት በተለይም የደቡባዊ ዓለምን የጋራ ጥቅም ለማስጠበቅ በተባበሩት መንግሥታትና እንደ ብሪክስ ባሉ መድረኮች በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!