የሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ከሚኖሩ ነዋሪዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያዩ ነው ፡፡
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አብዱልቃድር ረሺድ እንደገለጹት ÷ ውይይቱ በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች፣ በፀጥታና ልዩ ሃይል መልሶ መደራጀት እንዲሁም በሌሎች የልማት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡
አመራሮች በክልሉ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የወንዝ መሙላት ጉዳት የደረሰባቸውን የሸበሌ፣ አፍዴር፣ ሊባንና ዳዋ ዞኖች ጉብኝት ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህም በአደጋው ለተጎዱ ዜጎች እየተደረገ ያለውን ድጋፍ አመራሩ በልዩ ሁኔታ የተመለከተ መሆኑን አቶ አብዱልቃድር መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
እየጣለ ባለውከባድ ዝናብ ምክንያት በወንዞች አከባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ከጉዳት ለመከላከል የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የኢፌዴሪ አየር ኃይል ሰፊ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡