በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ሁሉን አቀፍ የፀጥታ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ሀገራት ሁሉን አቀፍ የፀጥታ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንዳለባቸው የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴኦዬ አሳሰቡ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች በአህጉሪቱ ወቅታዊ የሠላም ደኅንነት ጉዳዮች ላይ በአፍሪካ ኅብረት ዋና መስሪያ ቤት እየመከሩ ነው።
የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴኦዬ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ በአፍሪካ አሁንም አሳሳቢ የጸጥታ ችግሮች እና ስጋቶች አሉ ።
ሽብርተኝነት፣ አክራሪነትና ጽንፈኝነት፣ ሽምቅ ውጊያ፣ አመጽና ሌሎች የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎች በዋናነት የአህጉሪቱን የጸጥታ ሁኔታ ማባባሳቸውን ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ደግሞ የአህጉሪቱ የሰላም እጦት ላይ ተጨማሪ ጫና መፍጠራቸውን ጠቁመው ÷የህብረቱ ሀገራት ሰላምን ለማረጋገጥ ያወጧቸውን ስትራቴጂዎች በተከታታይ መገምገምና የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ከዚህም ባለፈ በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ለማስፈን ሀገራት ከተናጠል ሥራዎች ጎን ለጎን ሁሉን አቀፍ የፀጥታ ቅንጅታዊ አሰራርን ገቢራዊ ማድረግ እንዳለባቸው በውይይቱ ተነስቷል።
የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ማድረግ የሚቻለው በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ሲቻል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ÷ የአፍሪካ ኅብረትም ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በመሆኑም የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ዛሬ በተጀመረው ምክክር በጋራ የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች ወደ ተግባር ለመለወጥ ኅብረቱ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት በሱዳን ያለምንም ቅደመ ሁኔታ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ሥምምነት እንዲደረግ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑም ተነስቷል።
ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረውን ጦርነት በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ስር በሰላም የቋጨችበት መንገድ ለሌሎች ሀገራት አርዓያ ሊሆን እንደሚገባም ተጠቁሟል።
የመከላከያ ሚኒስትሮች እያካሄዱት ባለው ምክክር በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ፈንድን ለማጠናከርና የአፍሪካ ተጠባባቂ ኃይልን በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል የሚያስችል ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ኢዜአ ዘግቧል፡፡