ማህበራዊ እሴቶችን ለትውልዱ ለማስተላለፍ ቤተሰብ ጉልህ ሚና ሊወጣ ይገባል – ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ማህበራዊ እሴቶችን ጠብቆ በማቆየትና ለትውልዱ በማስተላለፍ ሂደት ውስጥ ቤተሰብ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅበት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገለጹ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የቤተሰብ ቀን ”የቤተሰብ ሚና ለትውልድ ስብዕና” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መርሐ-ግብሮች በአዲስ አበባ ተከብሯል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንዳሉት ÷ቤተሰብ የሀገር መሰረትና ዋልታና እንደ አንድ የተፈጥሮ መሰረታዊ ተቋም የሚወሰድ ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር ጉልህ አበርክቶ ያለው ነው።
በተለይም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለቤተሰባዊነት የሚሰጠው ክብር ልዩ መሆኑን ገልጸው ÷ ይህም ትውልዱ በመከባበር፣ በመቻቻልና አብሮ በመኖር የሚያምን እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ይሁንና ዘመናዊ የአኗኗር ዘዬው ያሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ ለቤተሰብ የሚሰጠው ዋጋና ክብር እንዲሸረሸር የማድረግ አዝማሚያዎች እየታዩ እንደሆነም ነው ያነሱት።
በተለይም ማህበራዊ ሚዲያ ትክክለኛውንና ነባሩን የቤተሰብ መሰረት የማሳጣት እድሉ ሰፊ መሆኑን ገልጸው ÷ቤተሰብ ማህበራዊ እሴቶችን ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡