የኦሮሚያ ክልል ጥሪት ያፈሩ አርሶና አርብቶ አደሮችን ወደ ኢንቨስተርነት የማሳደግ አሰራር መተግበር ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል በተለያየ መልኩ ጥሪት ያፈሩና አቅም የፈጠሩ አርሶና አርብቶ አደሮችን ወደ ኢንቨስተርነት ማሳደግ የሚያስችለውን መመሪያ አዘጋጅቶ መተግበር መጀመሩን አስታወቀ።
ክልሉ አጠቃላይ ወቅታዊ የኢንቨስትመንት አሰራሮች መሻሻልን አስመልከቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊና የክልሉ ኦዲት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳባ ደበሌ፥ ባለፉት ዓመታት የክልሉን ሕዝብ ኢኮኖሚ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
“በዋናነት የኢንቨስትመንት ሴክተሩን ማጠናከር ቀዳሚ መሆኑ ታውቆ ዘርፉን የማሻሻል ሥራ ተከናውኗል” ብለዋል።
እንደ አቶ ዳባ ገለጻ፥ በክልሉ ከ11 ሺህ በላይ ኢንቨስትመንቶች ያሉ ሲሆን፥ 51 በመቶ የሚሆኑት በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው።
በተጨማሪም 12 በመቶ በግብርና ዘርፍ፣ 18 በመቶ የግብርና ምርት በማቀነባበር እንዲሁም 17 በመቶ የሚሆኑት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የባለሃብቶች አጠቃላይ ሁኔታን ሲያብራሩም “92 በመቶ የአገር ውስጥ በለሃብቶች፣ 3 ነጥብ 2 በመቶ ዲያስፖራ እና 4 በመቶ የውጪ አገር ዜጎች ናቸው” ብለዋል።
ይሁን እንጂ በተለያየ መንገድ ጥሪት ያፈሩ አርሶና አርብቶ አደሮች እስካሁን በኢንቨስትመንት ዘርፉ በስፋት እንዳልተሰማሩም ነው አቶ ዳባ የገለጹት።
“የክልሉ መንግስት ይህን ለማስተካከልና ሌሎች የኢንቨስትመንት ማነቆዎችን ለመፍታት የሕግ ማሻሻያዎችን አድርጓል” ሲሉም ተናግሯል።
ከነዚህ ውስጥ አርሶና አርብቶ አደሩ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገባ የሊዝና የመሬት ኪራይ ክፍያ ነጻ የሚያደርግለት መመሪያ መውጣቱን ነው በማሳያነት የጠቀሱት።
ከዚህ ባለፈ በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው በተለያየ ዘርፍ ወደምርት ሥራ የገቡ የክልሉ ወጣቶችም የሚበረታቱበት መመሪያ መተግበር መጀመሩን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ዳባ ገለጻ የሕጉ መሻሻል ትክክለኛ አልሚ ባለሃብቶች ያለምንም እንግልት ወደሥራ እንዲገቡ ያደርጋል።
የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ኃይሉ ጃልዴ፥ “ኢንቨስትመንት የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ የውጪ ምንዛሬ የሚያመጣና ለቴክኖሎጂ ሽግግር በር የሚከፍት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል” ይላሉ።
አቶ ኃይሉ እንዳሉት የዘርፉ ማነቆ ሆነው የቆዩ የአሰራር ችግሮችን በመሰረታዊነት የመፍታት ሥራ ለመስራት የኢንቨስትመንት አስተዳደር ደንቡም እንዲሻሻል ተደርጓል።
ይህም ባለሃብቶች ብዙ ሳይንገላቱ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኙ የአንድ መስኮት አገልግሎት እንዲጀመር ማድረጉን ነው ያስረዱት።
“የአንድ መስኮት አገልግሎት ደግሞ 12 ሴክተር መስሪያቤቶች በአንድ ማዕከል ላይ እንዲገኙ አስችሏል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።