1 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
የ2015 በጀት ዓመት የሶስተኛው ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት እየተገመገመ ነው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል÷ አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የማምረት አቅምን ከ46 በመቶ ወደ 53 በመቶ በማድረስ የዕቅዱን 96 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
በሌላ በኩል ከውጭ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የምርት አይነቶች ተለይተው በተሰሩ ስራዎች 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትና የተወሰኑ ምርቶችን ደግሞ ወደ ውጭ መላክ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
የ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ መጀመሪያ ላይ 30 በመቶ ድርሻ የነበረውን የማምረቻ ዘርፍ የገበያ ድርሻ በዚህ ዓመት 34 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እስካሁን 37 በመቶ ማድረስ መቻሉንም አንስተው ቀጣይም የውጭ ምርቶችን ለይቶ በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት አሰራሮች ላይ በማተኮር ይሰራል ብለዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፥ ከውጭ የሚገኙ ምርቶችን ለመተካት በተሰሩ ስራዎች ስንዴንና የቢራ ግብስን ሙሉ በሙሉ፣ በሩዝ ደግሞ 50 በመቶ መተካት እንደታቸለ ጠቅሰው በቀጣይ ሶስት ዓመት ሩዝ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት እንደሚተካ አስረድተዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሤ፥ በታክስ ገቢ አሰባስብ በዘጠኝ ወራት የዕቅዱን 98 በመቶ በማሳካት አበረታች ውጤት እንደተገኘ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በቀጣይም ከዕቅድ ማሳካት ባሻገር በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል፣ ግብር ከፋዩን ማህበረሰብ ግንዛቤና የሕግ ተገዥነት በማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።