Fana: At a Speed of Life!

ፌዴራል ፖሊስን መቀላቀላችን ለላቀ ሀገራዊ ኃላፊነትና የህዝብ አገልግሎት እንድንዘጋጅ አድርጎናል – የቀድሞ ልዩ ኃይል አባላት

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፌዴራል ፖሊስን መቀላቀላችን ለላቀ ሀገራዊ ኃላፊነትና የህዝብ አገልግሎት እንድንዘጋጅ አድርጎናል ሲሉ የቀድሞ የክልሎች ልዩ ኃይል አባላት ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ወደ ፌደራል ፖሊስ ለተቀላቀሉ የቀድሞ ልዩ ኃይል አባላት የአቀባበል እና የስልጠና መርሐ ግብርን አስጀምረዋል።

በኢትዮጵያ ጠንካራና የተደራጀ የፖሊስና የመከላከያ ኃይል ለመገንባት በክልሎች የነበሩ ልዩ ሃይሎችን በመረጡት ሃይል ውስጥ እንዲቀላቀሉ በመንግስት ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።

በዚሁ ውሳኔ መሰረት ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ፌደራል ፖሊስን በመምረጥ በርካታ የቀድሞ የክልል ልዩ ሃይል አባላት ወደ ፌደራል ፖሊስ ተቀላቅለዋል።

በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ወደ ስልጠና ለመግባት አቀባበል ከተደረገላቸው መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ከድር መሃመድ እና አበባው ታደለ በሰጡት አስተያየት የፌዴራል ፖሊስን በመቀላቀላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው በሚኖራቸው የስልጠና ጊዜ ጥሩ የሙያ ክህሎት እንደሚያገኙ ያላቸውን እምነት የገለፁት የቀድሞው ልዩ ሀይል አባላት የፌዴራል ፖሊስን መቀላቀላችው ለላቀ አገራዊ ሃላፊነትና የህዝብ አገልግሎት እንዲዘጋጁ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ወደ ፌደራል ፖሊስ የተቀላቀሉት ብሩክ ንጉሴ እና ዋልቴ ካሳሁን ÷ከዚህ ቀደም በክልል ደረጃ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ደግሞ በፌዴራል ፖሊስ ሀገራዊ ተልእኮዎችን ለመፈፀም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በሙያቸው ዜጎችን በታማኝነት፣ በእኩልነት እና ፖሊሳዊ ስነ-ምግባርን አክብረው የሚሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የፖሊስ ዶክትሪን፣ ፖሊሳዊ ስነ-ምግባር፣ ወንጀል መከላከልና በሌሎችም ስልጠና የሚወስዱ ናቸው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.