ፍርድ ቤቱ ሲሳይ አውግቸው (ረ/ፕሮፌሰር) እና ወንዶሰን አሰፋን (ዶ/ር) ጨምሮ በ6 ግለሰቦች ላይ ለክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቀደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ በሽብር ወንጀል በተጠረጠሩ ሲሳይ አውግቸው (ረ/ፕሮፌሰር) እና ወንዶሰን አሰፋን (ዶ/ር) ጨምሮ በስድስት ግለሰቦች ላይ ለዓቃቤ ሕግ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ፈቀደ፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በቀዳሚነት የወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር፣ መሰረት ቀለመወርቅን (ዶ/ር) እና የገነት አስማማውን በሁለት መዝገብ የተካተቱ የዘጠኝ ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ተመልክቷል።
በዚህ መዝገብ ላይ ተጠርጣሪዎቹ ከጠበቆቻቸው ጋር ተገኝተዋል።
በመዝገቡ ላይ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በፖሊስ ሲከናወን የቆየውን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ክስ ለመመስረት የ15 ቀን ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ተጠርጣሪዎች በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ምርመራ ሲከናወንባቸው በቆዩባቸው ጊዜያት ምርመራውን ሲመራ እንደነበር ጠቅሰው፥ እንደ አዲስ መዝገቡን ተመልክቼ ክስ ለመመስረት 15 ቀን ይሰጠኝ ማለቱ ተገቢ አደለም ሲሉ ተከራክረዋል።
የምርመራ መዝገቡ ተዘግቶ ደንበኞቻችን ከእስር ይፈቱ ያሉት ጠበቆች፥ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ስርዓት መሰረት ክስ የመመስረቻ ጊዜ የሚሰጥ ከሆነ የዋስትና መብታቸው ይፈቀድ ሲሉም ጠይቀዋል።
ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ÷ ምርመራውን ሲመራ ቆይቶ እንደ አዲስ መዝገቡን ለመመልከት ተብሎ ክስ መመስረቻ ጊዜ መጠየቁ ተገቢ አደለም ለሚለው ለጠበቆች መከራከሪያ ነጥብን በሚመለከት የሽብር ወንጀልን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ወንጀሎች ምርመራን የመምራትና አቅጣጫ የማስቀመጥ ስልጣን እንደተሰጠው አብራርቷል።
ይህም ስልጣን በምርመራ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈፀምና ምርመራው ሕጋዊነቱን ጠብቆ አግባብ ባለው መልኩ እንዲከናወን እንመራለን አቅጣጫም እናስቀምጣለን ያለው ዓቃቤ ሕግ ይህ ማለት ግን ዝርዝር ማስረጃዎችን እናውቃለን ማለት አደለም ሲል መልስ ሰጥቷል።
የተጠርጣሪዎቹን ቆይታ በተመለከተ በጠበቆቻቸው አስተያየት አልተሰጠበትም በማለት ለችሎቱ የገለፀው ዓቃቤ ሕግ አስተያየት ባይሰጥበትም የሰው ህይወት የጠፋበት መዝገብ በመሆኑ በሥነ-ስርዓት ህጉ የዋስትና መብት ስለማያሰጥ ከፖሊስ የተረከብኩትን መዝገብ ተመልክቼ ክስ እስክመሰርት ድረስ ተጠርጣሪዎቹ በማረፊያ ቤት ይቆዩልኝ ሲል ችሎቱን ጠይቋል።
ተጠርጣሪ መሰረት (ዶ/ር) በመዝገቡ ሰው ሞቷል ተብሎ መገለጹ በሞራላቸው ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድርባቸው በመጠቆም ክቡር የሰው ልጅ ቀርቶ እንስሳት እንኳን እንዲሞት አንፈልግም ይህን ፍርድ ቤቱ ተገንዝቦ ያስቁምልን ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።
የችሎቱ ዳኛ በበኩላቸው÷ በጉዳዩ ላይ የሰው ሞት ስላለበት ይህን እናጣራለን በማለት በዓቃቤ ሕግ የተገለፀ ነጥብ መሆኑን ጠቅሰው ማብራሪያ ሰጥተውበታል።
3 ተኛ ተጠርጣሪ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደደረሰብን ያቀረብነው አቤቱታ በሚመለከት ምን ደረጃ ላይ ደረሰ? ሲሉ ለችሎቱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተገቢውን ማጣራት እና ምርመራ አድርጎ መልስ ለመስጠት ጊዜ ያስፈልገኛል በማለት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው በደብዳቤ ለፍርድ ቤቱ ማመልከቱን በችሎቱ ዳኛ መልስ ተሰጥቶበታል።
በተመሳሳይ በሌላ መዝገብ ጉዳያቸው የታየው ሲሳይ አውግቸው (ረ/ፕሬፌሰር)፣ ማዕረጉ ቢያብን (ረ/ፕሮፌሰር) እና ሄኖክ አዲስ የተባሉ ተጠርጣሪዎች መዝገብ ሲሆን ÷ በዚህ መዝገብ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በ3ቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ሲያከናውን የነበረውን ምርመራ አጠናቆ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን ገልጿል።
በዚሁ መዝገብ የተሰየመው ዓቃቤ ሕግ በእነ ወንደሰን (ዶ/ር) መዝገብ የጠየኩት የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጥያቄና ያቀረብኩት መከራከሪያ ነጥብ ይያዝልኝ ያለ ሲሆን÷ በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩልም በተመሳሳይ ያቀረብነው መከራከሪያ ነጥብ ይያዝልን ብለዋል።
ፍርድ ቤቱም ቀደም ብሎ በተመሳሳይ ጉዳይ የተነሳ የግራ ቀኙን የመከራከሪያ ነጥቦችን በዚህ መዝገብ እንዲያዝ አድርጓል።
አጠቃላይ የግራ ቀኙን ክርክር በመመርመር ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የስድስቱንም የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለዓቃቤ ሕግ ክስ የመመስረቻ የ15 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።
በእነ ሲሳይ (ረ/ፕሮፌሰር) መዝገብ ተካተው የነበሩት ተጠርጣሪ ሰለሞን ልመንህን ፍርድ ቤቱ የ10 ሺህ ብር ዋስትና መብት የፈቀደ ሲሆን÷ ነዋይ ዮሃንስን በሚመለከት ደግሞ በ20 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ ፈቅዷል፡፡
በሌላ በኩል በዚሁ መዝገብ ተካቶ የነበረው ተጠርጣሪ ጎበዜ ሲሳይን በሚመለከት መርማሪ ፖሊስ የምርመራ ስራውን አለማጠናቀቁን ገልጿል፡፡
ከዚህ በፊት በተሰጠው የ14 ቀን ጊዜ ውስጥ ማስረጃ መሰብሰቡን ጠቅሶ÷ ቀሪ የባንክ የገንዘብ ዝውውር ለማጣራት፣ የቀሪ ምስክር ቃል ለመቀበል፣ በምርመራ ቡድን እየተጣራ የሚገኝ የተጎጂዎችን ውጤት ለማምጣት እና መሰል ቀሪ ስራዎችን ለመስራት ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በኩላቸው፥ በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ የክስ መመስረቻ ጊዜ መጠየቁ የምርመራ ስራው መጠናቀቁን ያሳያል በማለት ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ እንደማይገባ ጠቅሰው ተከራክረዋል።
የተጠረጠረው በሙያው በሚዲያ በሰጠው ትንታኔ ምክንያት በመሆኑ ይህ ማስረጃ በቀላሉ ለማግኘት ስለሚያስችል ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ አግባብነት የለውም ሲሉም ተከራክረዋል።
ውጭ ሃገር መሸሽ ስለማይችል ከሀገር እንዳይወጣ እግድ ተጥሎ የዋስትና መብቱ ይፈቀድለት ሲሉም ጠይቀዋል።
መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ፥ ”የተጠረጠረው በሙያው ሳይሆን አንዱ ህዝብ በአንዱ ላይ እንዲነሳ በመቀስቀስና፣ የሚዲያ የፕሮፖጋንዳ ክንፍ ተብሎ በተቋቋመ መዋቅር ውስጥ ባደረገው ተሳትፎ በሽብር ወንጀል መነሻ ነው የታሰረው ”ሲል መልስ ሰጥቷል።
በተጨማሪም መርማሪው ተጠርጣሪው ከዚህ በፊት ወደ ውጭ ሀገር ሊሸሽ ሲል መያዙን ጠቅሶ÷ አሁንም ቢወጣ ሕግን አክብሮ ላይቀርብ ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄውን በመቃወም ተከራክሯል።
ተጠርጣሪ ጎበዜ ሲሳይ በበኩሉ÷ ከዚህ በፊት በቀረበበት ክስ ነጻ መውጣቱን ጠቅሶ ጉዳዬ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ይታይልኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
በጎበዜ ሲሳይ ላይ ከዚህ በፊት በተሰጠ የ14 ቀን ጊዜ የተሰራውን የምርመራ መዝገብ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ በተነሳው ክርክርን መርምሮ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መስጠት አስፈላጊነትን በማመን የ12 ቀን የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ