የኢትዮጵያ “የሰላም ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት” ተመሠረተ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ሰላም ዙሪያ የሚሰሩ 50 ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች “የሰላም ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት” በይፋ መሰረቱ።
የሰላም ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ዛሬ ሲመሰረት ሦስት የጠቅላላ ጉባዔ እና ሰባት የቦርድ አባላትን መርጧል።
ኅብረቱ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ የዜጎች መብቶች እንዲከበር ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመሥራት ዓላማ አድርጎ የተመሰረተ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በሰላም፣ በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ግንባታ ላይ በማተኮር ግጭቶችን ቀድሞ መከላከልና ሲፈጠሩም በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ያደርጋልም ተብሏል፡፡
የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ታዬ ደንደአ÷ ለኢትዮጵያ ከሰላም የሚበልጥ ጉዳይ ስለሌለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ተቋም እንዲሆን አሳስበዋል፡፡
የኢፌዴሪ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው÷ ኅብረቱ ሀገራዊ ምክክር መድረኩንና የሰላም ሂደቱን በማሳካትና በማጽናት አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
ሰላምን ለማስጠበቅ ከፌደራልና የክልል መንግስታት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሀገርና ሕዝብ ሰላም እንዲከበር የግንዛቤና የንቅናቄ ሥራዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታልም ነው ያሉት።
ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ስራ ላይ ማዋል፣ ለሰላም ግንባታ አጋዥ ስትራቴጂዎችን መለየትና መተንተን ከህብረቱ አባላት ይጠበቃል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡