ሙስና በመቀበል በተጠረጠሩ የከተማ አስተዳድሩ ሠራተኞች ላይ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘‘መሬት እናሰጣለን’’ በማለት ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ሙስና ተቀብለዋል በተባሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሦስት ሠራተኞች ላይ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።
ተጠርጣሪዎቹ ÷ 1ኛ የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት የግንባታ ቁጥጥር ባለሙያ ፍቅረስላሴ ታደለ፣ 2ኛ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከተማ አስተዳደር የአቤቱታና ቅሬታ ምርመራ ዘርፍ ዳይሬክተር ታምራት እስጢፋኖስን እና የየካ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር የመብት ፈጠራ ቡድን መሪ ዘውዱ ደገፋ ይባላሉ።
መርማሪ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ሲያከናውን የቆየውን ምርመራ መዝገብ ለዓቃቢ ህግ ማስረከቡን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስታውቋል።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዓቃቢህግ ተጠርጣሪዎቹ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አራራት ሆቴል ጀርባ ‘‘5 ሺህ ካሬ ሜትር ባዶ ቦታ እንሰጣለን’’ በማለት አስቀድመው 30 ሚሊየን ብር ሙስና ገንዘብ ከጠየቁ በኋላ ከሁለቱ የግል ተበዳዮች 10 ሚሊየን 250 ሺህ ብር ተቀብለዋል ሲል ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያው ላይ አብራርቷል።
በተጨማሪም 1ኛ እና 2ኛ ተጠርጣሪ የሜሪዲያን ሆቴል ባለቤት ለሆኑት ግለሰብ በሆቴሉ ስም የተመዘገበ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የመከነ ቢሆንም በይዞታው ላይ 1ሺህ 600 ካሬ ሜትር ጭማሪ እንደተደረገላቸው የሚያሳዩ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን ለግል ተበዳይ ማሳየታቸውን ጠቅሶ ዓቃቢህግ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያው ላይ አስረድቷል።
በዚህ መልኩ ተጠርጣሪዎቹ ሲገለገሉበት ቆይተዋል የተባሉበትን ሀሰተኛ የከተማ አስተዳደሩ ሰነዶችን በ1ኛ ተጠርጣሪ መኖሪያ ቤትና በ2ኛ ተጠርጣሪ በሚያሽከረክረው ተሽከርካሪ ውስጥ በብርበራ መገኘቱን እንዲሁም በ1ኛ ተጠርጣሪ መኖሪያ ቤት ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችን የተያዙ መሆኑን ዓቃቢህግ ለጊዜ ቀጠሮ አቅርቧል።
በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 109 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠውና ተጠርጣሪዎቹ በማረፊያ ቤት እንዲቆዩለት ዓቃቢ ህግ ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው ÷ ተጨማሪ ጊዜ መሰጠት የለበትም ፤ የዋስትና መብታችን ሊከበር ይገባል የሚሉ መከራከሪያ ነጥቦች ተነስተዋል።
ክርክሩን የተከታተለው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ በስነ ሥርዓት ህጉ መሰረት የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ለዓቃቢህግ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ