ውስብስብ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ መፍትሔዎቹ ላይ በጋራ መስራት ይገባል – አቶ ማሞ ምህረቱ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ላጋጠሟት ውስብሰብ ኢኮኖሚያዊ ችገሮች መሰረታዊ መፍትሔ ለማፍለቅ ያለመ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡
የፓናል ውይይቱ÷ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ በገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ነው የተካሄደው፡፡
ፓናሉን የከፈቱት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)÷ ገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪዎች የፖሊሲ አማራጮችን በማዘጋጀት እና የመፍትሔ ሐሳቦችን በማመንጨት ለፖሊሲ አውጪዎች አጋዥ የሚሆን ሥራ እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቅረፍ የሚያግዝ እና በሀገሪቱ አዲስ እይታ የሚያሰፍን ሥራ ለመሥራት ገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት ሚና የላቀ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
ገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ከተለያዩ ምንጮች በሳይንሳዊ መንገድ የተጠና እና የተነተኑ መረጃዎችን በማዘጋጀት ለትክክለኛ ውሳኔ የሚያበቃ መረጃ ማመንጨት እንደሚገባቸው አንስተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከገለልተኛ ፖሊሲ አማካሪዎች የሚገኘውን በማስረጃ የተደገፈ እና ለመሰረታዊ ለውጥ የሚያግዝ መረጃዎችን መጠቀም እንደሚገባው በውይይቱ ተነስቷል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው÷ ውስብስብ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት በተናጠል ሳይሆን በጋራ ጥረት እና ጉልበት መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የትኛውም መረጃ የተተነተነ እና ሀቀኝነቱ የተረጋገጠ ማድረግ ከተቻለ በኢትዮጵያ የሚፈልገውን ቀጣይነት ያለው ለውጥ እና እድገት ማምጣት ይቻላል ሲሉ ማብራራታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።